ወረርሽኙ የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል ዘርፍ የማዘዋወሩን ሂደት አዘግይቶታል

94

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ወረርሽኝ የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ስራ እንዲዘገይ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ፕሮጀክቶቹን ለማዘዋወር በሰኔ ጨረታ ይወጣል ተብሎ ነበር።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ለኢዜአ እንዳሉት የኮሮና ወረርሽን በአገሪቷ በመከሰቱ ወደ ፋብሪካዎቹ በመሄድ የአካባቢ ጥናት እንዳይካሄድ እክል ፈጥሯል።

ይሁንና ለወረርሽኙ ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ ጥናቱን በጥንቃቄ በሚካሄድባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ያነሳሉ።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ፋብሪካዎቹን ወደ ግል እንዲዘዋወሩ መደረጉ የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ለአገረቷ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ፋይዳ ይኖረዋል።

ፋብሪካዎቹን ወደ ግል የማዘዋወሩ ሂደትም ጥንቃቄ የተጠናና የአገሪቷን ምጣኔ ሃብት ዕድገት በሚያረጋግጥ መልኩ መከናወኑንም አስረድተዋል።

አሁን በምርት ላይ ካሉት መተሃራ፣ ወንጂና ፊንጭአ ስኳር ፋብሪካዎች ውጭ 13ቱ ፋብሪካዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ይናገራሉ።

የገንዘብ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ኢዮብ ታዬ በበኩላቸው ለረጅም ዓመታት በመንግሥት ተይዘው የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወሩ ሂደት ለኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

በተለይም አገሪቷ በተደጋጋሚ ለሚያጋጥማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል ይላሉ።

መንግሥት ወደ ግል ዘርፉ ከሚያዘዋውራቸው ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣13 የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ይጠቀሳሉ። 

ወደ ግል ከሚዘዋወሩት የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ተንዳሆ፣ኦሞ ኩራዝ፣አርጆ ዴዴሳ፣ኦሞ ኩራዝና ከሰም ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም