ህብረተሰብ ኮሮናን ለመከላከል የጀመረውን ስራ ሳይዘናጋ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰብ ኮሮናን ለመከላከል የጀመረውን ስራ ሳይዘናጋ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
ግንቦት 14/2012(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ህብረተሰብ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጀመረውን ስራ ሳይዘናጋ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ጥሪ አቀረበ።
በግብረ ኃይሉ የአደጋ ጊዜ ተግባቦትና ማህበረሰብ ንቅናቄ ንዑስ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ሬድዋን መሐመድ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ከኢድ አልፈጥር በዓል ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ በሚያከናውነው ግብይትና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
ህብረተሰቡ በእውቀት በመመራት ሳይዘናጋ ቫይረሱን የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
"በክልሉ የተቋቋመው የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይልም የጀመረውን የቅስቀሳ እና የቤት ለቤት ልየታ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል" ብለዋል።
የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ. ም በጋራ ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ውስጥ አንድ ግለሰብ ከሐረሪ ክልል ነው።
በዚህም ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 15 ግለሰቦችና የጤና ባለሙያዎች ለጥንቃቄ በክልሉ ወደ ተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን አቶ ሬድዋን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡም በዚህ ሳይደናገጥና በቸልተኝነት ሳያልፍ የጀመረውን እራስን የመከላከል ተግባር መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ይፋ ያደረጉት ቫይረሱን የመከላከያ ዘዴዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በተደጋጋሚ በውሃና ሳሙና መታጠብ፣ አስገዳጅ ካልሆነ በቤት ውስጥ መቆየት፣ ከቤት ወጥተው ሲንቀሳቀሱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ነው።
ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦች ሪፖርት ለማድረግ ደግሞ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም 952 መጠቀም እንደሚቻል ተመልክቷል።