ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አል ፈጥር በዓልን ሲያከብር ከኮሮናቫይረስ እንዲጠነቀቅ የጤና ሚኒስትሯ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል-ፈጥር በዓል ሲያከብር ለኮሮሮና ቫይረሰ ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንዳለበት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒሰትሯ 1441ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ህዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ጾም ወቅት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚያግዝ መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄ ማሳለፉን አንስተዋል።

የኢትዮያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በመቀበል የጁማአ ጀመአ ስግደትን በመተው በተጠናጠልና በቤት ውስጥ ሲሰግዱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ለሚደረግው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸው ለመላው የእምነቱ ተከታዮች ምስጋና አቅርበዋል።

የሚደረገው ጥንቅቄ በኢድ በአል አከባበር ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።         

በተለይም በበዓል ወቅት እንቅስቃሴዎች ስለሚበዙ በማንኛውም ጊዜ የፊት ጭንብሎችን በማድረግና የእጅ ንጽህናን መጠበቅ እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።             

በበዓሉ ወቅት የሚበሉ ምግቦችን አብስሎ መመገብ እንደሚገባና እርድም በከፍተኛ ጥንቃቄ  መከወን እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዳስታወቀው 1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ዛሬ ምሽት ጨረቃ ከታየች ቅዳሜ ካልሆነም እሁድ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም