ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ 20 የመሬት ይዞታዎችን የመለየትና ቅየሳ ስራ በመገባደድ ላይ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ የሚገኙ 20 የመሬት ይዞታዎች የሙከራ የይዞታ መለየትና መቀየስ ስራ ክንውን 95 በመቶ መድረሱን አስታወቀ።

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በመላ ሃገሪቷ ያለውን የፌዴራል መሬት ይዞታን ለማልማትና ለማስተዳደር ያመች ዘንድ የመሬት መረጃዎችን ለማሰባሰብና የይዞታ ካርታ ስራ ማከናወን ጀምሯል።

ኮርፖሬሽኑ በመጋቢት 2012 ዓ.ም ከጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር "ለፌዴራል መሬት ይዞታዎች ካርታ ዝግጅት" የመግባቢያ የሰነድ ስምምነት  በመፈራረም ስራው በፕሮጀክት ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ወደ ስራ መግባቱም ይታወሳል፡፡

የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ደረጃ ሂደት የገመገሙት የተቋማቱ ሃላፊዎች በአዲስ አበባ ንዑስ ፕሮጀክት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ 200 የመሬት ይዞታዎች መካከል በ20 የመሬት ይዞታዎች የሚካሄደውን የሙከራ የይዞታ መለየትና መቀየስ ስራ ተመልክተዋል።

በእቅድ መሰረት 19 ለሚሆኑት የድንበር መለየትና የኮኦርድኔት ነጥቦችን መልቀም ፣ በይዞታው ስር ያሉትን የህንጻ አገልግሎት መለየትና መመዝገብ እንዲሁም የቁራሽ መሬቶችን መልክአ ምድራዊ ስራዎች ክንውን ተገምግሟል።

በዕቅዱ መሰረት የመስክ ሥራው አፈፃፀም እስካሁን 95 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን የተቋማት አለመተባበር፡ የመረጃ እጥረት እንዲሁም በወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በሂደቱ ላይ ፈተና መሆኑ ተመልክቷል።

በክንውኑ ወደ ቀጣይ ምእራፍ ለመግባት ሃላፊዎቹ የስራ አቅጣጫዎችን ማስቀመጣቸውን ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተለዩት ይዞታዎች መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ይዞታዎች ይገኙበታል፡፡

የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን መሬት እንዲያስተዳድር በአዋጅ የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም