'ትውልድን በትምህርት የመገንባት ስራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው - ኢንጂነር ታከለ ኡማ

152

አዲስ አበባ   ግንቦት  13/2012 (ኢዜአ) ትውልድን በትምህርት የመገንባት ስራ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ገለጹ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በእጅጉ ከተጎዱ ዘርፎች መካከል ትምህርት አንዱ ነው።

እንደተቀረው ዓለም ሁሉ በኢትዮጵያም ቫይረሱ ተገኘ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም እስከ መጀመሪያ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው በቤታቸው ተቀምጠዋል።

ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን የትምህርት መርሃ ግብር ሲሰጥ ቆይቷል።

ዛሬ በአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን ከሚሰራጨው ትምህርት በቤቴ መርሃ ግብር ጎን ለጎን "የይሳተፉ ይሸለሙ" የጥያቄና መልስ ውድድር በመሳተፍ ያሸነፉ ተማሪዎች ተሸልመዋል።

ሽልማቱን ለተማሪዎቹ የሰጡት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትውልድን በትምህርት የማነጽ ስራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለተማሪዎቹ የወጣውን መዋዕለንዋይ ከአንድ ህንጻ መገንቢያ ጋር ያነጻጸሩት ምክትል ከንቲባው በልጆች ላይ ኢንቨስት ያላደረገ ህዝብና መንግስት የሚቀጥለውን አገሩን በሚገባ አያውቀውም ብለዋል።

በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት በማስቀረት የነገ የአገር ተስፋ የሆኑትን ተማሪዎች ትኩረት ሰጥቶ ማስተማር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ልህቀትና በትውልድ ግንባታ ከቢሮው ጋር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ በቤታቸው ሆነው ትምህርት እየተከታተሉ ለሚገኙ ተማሪዎች የተበረከተው ሽልማት ተማሪዎችን ለመደገፍና ለወላጆችም እውቅና ለመስጠት ታስቦ ነው ብለዋል።

ከተሸላሚቹ መካከል የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ስህነ-ማሪያም ሲሳይ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪው ሙኒር ጀማል ሽልማቱ በቤት ውስጥ ሆነው ለሚማሩት ትምህርት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

ሌሎች ተማሪዎችም በቤት ውስጥ ሆነው በቴሌቪዥን የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት በመከታተል የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክረዋል።

የተማሪ ስህነ-ማሪያም አባት አቶ ሲሳይ ይልማ መርሃ ግብሩ ተማሪዎች በተቸገሩበት ወቅት መጀመሩን አድንቀው ለተማሪዎች እየተደረገ ላለው እገዛ አመስግነዋል።

ሌላዋ ወላጅ ወይዘሮ ሄለን ንጉሴም ለተማሪዎቹ በቤት ውስጥ እየተሰጠ ያለው ትምህርት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ያለው ድጋፍች ይበል የሚያሰኝ ነው፤ ጅማሮውም መልካም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም