ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ወረርሽኙን ለመከላከል የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጠ

ሐዋሳ፣ ግንቦት 13/2012( ኢዜአ) በደቡብ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት ላቅ ያለ የገንዘብና ዓይነት ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶችና ተቋማት እውቅና ተሰጠ።

የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል  ዛሬ ባዘጋጀው  ስነስርዓት እውቅና የተሰጠው በግንባታ፣ንግድ፣ ባንክና ሌሎችም መስኮች ለተሰማሩ  ነው።

የግብረ ኃይል ሰብሳቢና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት ድጋፉ ለወገን ደራሽ ወገን ነው የተባለው በተግባር የታየበት ነው።

"በተለይ ወረርሽኙ ዜጎች ባለቸው አቅም ሁሉ ትብብርና ድጋፍ ያሳዩበት የመረዳዳት፣የመደጋገፍና የመተዛዘን ባህላችን ጎልቶ የታየበት ክስተት ነው " ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከንግዱ ማህበረሰብ፣  ባለሀብቶች፣አርሶ አደሮችና ከመንግስት ሰራተኞች ከ318 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በገንዘብና ዓይነት መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ድጋፍ ከሰጡት  መካከል የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወረርሽኙ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም በፍጥነት የምርት ሥርዓቱን ቀይሮ አፍ መሸፈኛ ማስክን ጨምሮ ሌሎችንም ግብዓቶች  በማምረት የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የእውቅና አሰጣጡም  ዓላማ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ለማቅረብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ርስቱ " ይህን ክፉ ጊዜ እስክናልፍ ድረስ መደጋገፉ መቀጠል ይኖርበታል " ብለዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው መካከል የደቡብ ግሎባል ባንክ ቦርድ ተወካይ አቶ መላኩ ገዙ  ከክልሉ ግብረ ኃይል ጋር በመተባበር በተለያዩ ባንኮች የድጋፍ ማሰባሰቢያ የሂሳብ ቁጥሮች በመክፈት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያቅሙን  እንዲደግፍ   ሰፊ የሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህ አንገብጋቢ ወቅት የሚደረገው ድጋፍ ለማጠናከርም ባንኩ ከዚህ በፊት ካበረከተው 2 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ዛሬም አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የባለሀብቶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ካሚል ሃምዛ ማህበሩ በፓርኩ ውሰጥ ለሚገኙ 35 ሺህ ሰራተኞች  የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት በማቅረብና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ወረርሽኙን ለመከላከል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስካሁን  ለማህበረሰቡ፣ ክልሉና ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አንድ ሚሊዮን 500 ሺህ  ብር የዓይነት ድጋፍ በማድረግ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ዛሬም  300 ሺህ ብር የሚገመት የፊት መሸፈኛ ጭንብል ለክልሉ  ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል  ድጋፍ ማድረጋቸውን  አስታውቀዋል።

አስተዋጽኦ ላደረጉት ተቋማትና ደርጅቶች  የተሰጠው እውቅና የምስክር ወረቀት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም