የሐማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማህበር የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሐማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማህበር የዱቄትና ዘይት ድጋፍ አደረገ
ሐረር ፣ ግንቦት 13/ 2012 (ኢዜአ) በሐረር ከተማ የሚገኘው የሐማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማህበር ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ ዱቄትና ዘይት በክልሉ ለተቋቋመው ገቢ ማሰባሰብና ሀብት ማፈላለግ አብይ ኮሚቴ አስረከበ።
የምግብ ዱቄቱንና ዘይቱን ያስረከቡት የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ድጋፌ “የፍቅር ማዕድ” በሚል ስያሜ የተደረገው ድጋፍ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለችግር ለተጋለጡ 700 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች የሚከፋፈል ነው ።
ድጋፉ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።
በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ገቢ ማሰባሰብና ሐብት ማፈላለግ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም አክሲዮን ማህበሩ ላደረገው ደጋፍ ምስጋና አቅርበው የምግብ እህል እና የዘይት ድጋፉ አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኞችን ከመደጎም አንፃር አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
በተለይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ በቤት እንዲቆዩ ለማድረግም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያበረክታል ብለዋል።
ይህንን የበጎ አድራጎት ስራ ሌሎች ድርጅቶች፣ባለሀብቶችና ግብረ ሰናይ ተቋማትም አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ጥሪ አቅርበዋል ።
በተያያዘ ዜና በሀረሪ ክልል የኤች አይ ቪ /ኤድስ በደማቸው ያላባቸውን አባላት ያቀፉ 3 ማህበራት በኮሮና ቫይረስ ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለመደገፍ 50 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ ለአብይ ኮሚቴው አስረክበዋል።
የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት፣ኔፕላስ፣ተስፋ ብርሃንና መድህን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ማህበራት ናቸው ።
ማህበራቱን ወክለው ንግግር ያደረጉት አቶ አወቀ መብቱ እንደገለፁት የህዝብ ችግር የእኛም ችግር በመሆኑ እርስ በርስ ካልተደጋገፍንና ካልተረዳዳን ይህን ወቅት መሻገር ስለማይቻል የበኩላችንን ለመወጣት ስንል ድጋፉን አበርክተናል ብለዋል ።