ቀጥታ፡

በአምቦ አቅም ለሌላቸው 1 ሺህ 700 ሴቶች ድጋፍ ተደረገ

አምቦ ፣ ግንቦት13/2012 (ኢዜአ)   በአምቦ ከተማ አቅም ለሌላቸው 1 ሺህ 700 ሴቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር እንዳይጋለጡ የምግብ እህልና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ለችግር ለተጋለጡ ችግረኛ ሴቶች ድጋፉን ያደረጉት  'ስታንድ ፎር ቨርነረብል" የሚባል በጎ አድራጊ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ ዳይረክተር አቶ ምስጋናው ኢቲቻ  ዛሬ በአምቦ ከተማ ተገኝተው ግምቱ ከ573 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ከአንድ መቶ ኩንታል በላይ በቆሎና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አስረክበዋል ።

ድጋፉ ቫይረሱን በአገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ በሙሉ መከላከል እስኪቻል ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የአምቦ ከተማ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ሃጫሉ ገመቹ በስነ ስርአቱ ላይ ድርጅቱ ላደረገው የበጎ አድራጎት ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሽታውን መከላከል የሚቻለው እራስንና አካባቢውን በጋራ በመጠበቅና በመተጋገዝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአምቦ ከተማ  ሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ታደለች አለማየሁ በበኩላቸው "ነገ ሀገራችንን ማገልገል እንድንችል ዛሬ እራሳችንን ከበሽታው መጠበቅ አለብን" ብለዋል፡፡

እናት ሁሉንም ማድረግ ትችላለች ያሉት ኃላፊዋ  እናቶች ልጆቻችሁንና አካባቢያችሁን በመጠበቅ የነገ ሰው እንዲሆኑ መትጋት አለባችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ሴቶች መካከል የከተማው የያኢ ገዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጌጤ ኦልቀባ  እንዳሉት ከዚህ በፊት በአነስተኛ የመንገድ ላይ ሸቀጣ ሸቀጥ  የእለት ጉርሳቸውን ይሸፍኑ እንደነበር አስታውሰው ድጋፉ በኮሮና ምክንያት ለተዳከመው ገቢያቸው ማካካሻ እንደሚሆን ተነግረዋል።

ሌላኛው ድጋፍ የተደረገላቸው የፋሪሲ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እጅጋየሁ ሰይፉም ከወረርሽኙ በፊት በምግብ ቤት ተቀጥረው በመስራት ይተዳደሩ እንደነበር ገልጸው ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ስራ በማቆማቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

አሁን ግን  60 ኪሎ ግራም የምግብ እህል በማግኘታቸው የእለት ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው በማውሳት ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም