ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ተጨማሪ ዘጠኝ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰአት በተደረገ 3 ሺህ 747 የላቦራቶሪ ምርምራ ዘጠኝ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 398 ደርሷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ምላሽ አሰጣጥ  አስመልክቶ በጋራ በሚያወጡት መግለጫ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ስምንት ወንድና እና አንድ ሴት ሲሆኑ ከ20 እስከ 49 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 3 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሁለት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውና አንድ ሰው የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያለው ነው።

ሁለት ሰዎች ከአማራ ክልል የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በመተማ ለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሲሆን በአፋር ክልል በቫይረሱ የተያዙት ሁለት ሰዎች ደግሞ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው እንደሆነ በመግለጫው ተገልጿል።

አንድ ሰው ከሶማሌ ክልል የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያለው በጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ ያለ፤ አንድ ሰው ከትግራይ ክልል የውጭ አገር የጉዞ ታሪክና በማይካድራ ለይቶ ማቆያ የሚገኝ እንደሆነ ተመልክቷል።

ትናንት ከአዲስ አበባ አንድ ሰው ከበሽታው በማገገሙ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 123 ደርሷል።

ከግንቦት 10 እስከ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት አራት ቀናት ውስጥ 12 ሺህ 253 የላቦራቶሪ ምርምራ ተደርጎ 80 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል።

የያዝነው ሳምንት ሳይጠናቀቅ በአራቱ ቀናት በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ባለፈው ሳምንት ከግንቦት 3 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ከተያዙ ሰዎች አንጻር በሁለት ሰው ብልጫ አለው።

ከግንቦት 3 እስከ 9 ቀን 2012 ዓ.ም 22 ሺህ 394 የላቦራቶሪ ምርምራ ተደርጎ 78 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው መገለጹ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ እስካሁን 69 ሺህ 507 የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ 268 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ህክምና ውስጥ ይገኛሉ።

በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኝ ታማሚ የለም።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ አምስት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ሁለት ጃፓናውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም