ቀጥታ፡

''አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወረርሽኙን እናቆማለን ብሎ የሚናገር ሳይንቲስትም፣ የአገር መሪም አገርም የለም'' ... ዶክተር ኤባ አባተ

 አዲስ አበባ፤  ግንቦት 13/2012 (ኢዜአ) ''አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኮሮናቫይረስ   ወረርሽኝን እናቆማለን ብሎ የሚናገር ሳይንቲስትም፣ የአገር መሪም፣ አገርም የለም'' ሲሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ተናገሩ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ መሆኑን ተከትሎ በኢትዮጵያም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።

ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የነበረው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲራዘም ተደርጓል።

ምርጫው በመራዘሙ የህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ በመቅረቡ በጉዳዩ ላይ የባለሙያዎች ማብራሪያ እየተጠየቀ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

በዚህ መሰረት በዛሬው እለት የህገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ላይ ያተኮረ የባለሙያዎች ማብራሪያ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በመገኘት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስለሚገኝበት ሁኔታ ማብራሪያ ከሰጡት የጤና ዘርፍ ሃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቫይረሱን ማቆም የሚችል ማንም አካል አለመገኘቱን ገልጸዋል።

''አገራዊ ምርጫው በወረርሽኙ ምክንያት መዘግየቱ ይዞት የሚመጣውን ተጽኖ ለማስቀረት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው'' ብለዋል።

''ምርጫ የራሱ የአሰራር ሂደቶች አሉት'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መሰባሰብን የግድ የሚሉ ጉዳዮች ስላሉት ለወረርሽኙ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ከዚህም አልፎ  ምርጫውን ለመዘገብ ከቦታ ቦታ የሚሄዱ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት በመሆኑ የወረርሽኙን ተጋላጭነት እንደሚጨምር አስገንዝበዋል።

''ትናንት ቤታችን አልነበረም ዛሬ ቤታችን ገብቷል'' ያሉት ዶክተር ኤባ፤ ወረርሽኙ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

''አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወረርሽኙን እናቆማለን ብሎ የሚናገር ሳይንቲስትም የአገር መሪም አገርም የለም'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ''የገዘፈና ትልቅ የሆነ ችግር እየመጣ ባለበት ወቅት ትኩረታችንን ወደ መከላከሉ ማድረግ አለብን'' ብለዋል።

በሽታው ተወግዷል፣ ወይም መቋቋም የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል የሚለውንም ውሳኔ የሚያስተላልፈው የዓለም ጤና ድርጅት እንደሆነ ጠቁመዋል።

''በመሆኑም ሁሉም በጋራ ወረርሽኙን ለመግታት መረባረብ አለበት'' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም