ማህበሩ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ሙያዊ ኃላፊነቴን እወጣለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ሙያዊ ኃላፊነቴን እወጣለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ አባላቱ ሙያዊ አስተዋጽኦ እንደሚወጡ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር አሳሰበ።
የኮሮና ቫይረስን በመስጋት በቤት መውለድ አይገባም ብሏል።
ማህበሩ 28ኛውን የሚድዋይፎች ቀን በአለርት ሆስፒታል አክብሯል።
በአገልግሎት ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣አልባሳትና መሰል ግብአቶችን በስጦታ አበርክቷል።
የማህበሩ የቦርድ አባል አቶ ጀንበሬ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ማህበሩ እናቶች በጤና ተቋማት ጥንቃቄና ክብካቤ በተሞላበት ሁኔታ እንዲወልዱ ይሰራል።
ወላዶች ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረባቸውን ስጋትና ፍርሃታቸውን አስወግደው በተቋማቱ ክትትላቸውን እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
በአለርት ሆስፒታል የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስትና የእናቶች የማዋለጃ ክፍል ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ ጉልቦ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የእናቶችን የወሊድ አገልገሎት በሚመለከት በጥንቃቄ መሆኑን ገልጸው እናቶች ያለ ስጋት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ አብራርተዋል።
በተለይም የመውለጃ ጊዜአቸው የደረሰና በተያያዥ የጤና እክል በቤታቸው ያሉ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የራሳቸውንና የሚወልዷቸውን ህጻናት ጤንነት ለመጠበቅ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት።
በሆስፒታሉ ያሉ የጤና ባለሙያዎችም አገልግሎቱን በጥንቃቄ ለመስጠት 24 ሰዓት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ቤተልሔም ታዬ እንደሚሉት እናቶች በቅድመ ወሊድ ወቅት ቢያንስ ለአራት ጊዜ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ይህንንም በስፋት ለመተግበር በከተማዋ ባሉ ሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች አገልግሎቱ በስፋት እንደሚሰጥ ገልጸው የዘርፉ ባለሙያዎችም ክትትሉን እየሰጡ ናቸው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ኮቪድ-19 መከሰቱ ተከትሎ በጤና ተቋማቱ ይሰጥ የነበረው የወሊድና የቅድመ ወሊድ አገልግሎት እየተቀዛቀዘ መጥቷል ብለዋል።
ነገር ግን ቢሮው ለጤና ተቋማትና ለባለሙያዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና አስፈላጊ የህክምና ግብአቶችን አሟልቶ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁነቱን አዳብሯል።
ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን አክለው እናቶች ያለ ስጋት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በከተማዋ በአንድ ጤና ጣቢያ 10 ሚድዋይፎች የተመደቡ ሲሆን በሆስፒታሎች ደግሞ ከ 40 በላይ የሚድዋይፍ ባለሙያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በመስጋት በርካታ እናቶች በቤት ውስት እየወለዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም እናቶች ለደም መፍሰስና ለተያያዥ ችግሮች እየተጋለጡ ሲሆን ጨቅላ ህጻናትም እንደተወለዱ ማግኘት ያለባቸውን እርዳታ እንዳያገኙ ሆነዋል።
በእናቶችና በጨቅላ ህጻናት ሞት ቅነሳና ደህንነት ላይ የነበረው ውጤታማነት ሊያሽቆሎቁል ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተጠቁሟል።