በደቡብ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ቤቶች ልየታ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ቤቶች ልየታ ተደረገ
ሐዋሳ ፣ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እየተከናወነ ባለ የአሰሳ ሥራ የአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ቤቶች ልየታ መደረጉን የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ አባልና የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሣሙኤል ዳርጌ ለኢዜአ እንደተናገሩት ወረርሽኙን ለመከላከል የቤት ለቤት ልየታ ሥራው በሁሉም የደቡብ ክልል ወረዳዎችና ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
እስካሁን በተካሄደው እንቅስቀሴ የአንድ ሚሊዮን 500 ቤቶች ላይ የልየታ ሥራ መከናወኑን ገልጸው በዚህም ከስድስት ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ሰዎች ማዳረስ መቻሉን አስረድተዋል።
ይህም በቤተሰብ ደረጃ 38 በመቶ በግለሰብ ደግሞ 33 በመቶ መሸፈን እንደተቻለ ተናግረዋል።
ቅዳሜና እሁድ እስከ 36 ሺህ ቤቶች በሌሎች ቀናት ደግሞ እስከ 150 ሺህ ቤቶች አሰሳው እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ቤት ለቤት ልየታው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሣሙኤል "ኅብረተሰቡ በይበልጥ ተጋላጭ የሆነባቸው በተለይ በድንበር በሮችና በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በተገኙባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ሥራው እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በክልል ደረጃ የምርመራ ማዕከላት ሐዋሳና ወላይታ ሶዶ ላይ እንዳሉ አስታውሰው ተጨማሪ ማዕከል በአርባ ምንጭ ከተማ ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የጤና መምሪያ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ አባል የሆኑት አቶ ቡሪሶ ቡላሾ በበኩላቸው በሐዋሳ ስምንቱም ክፍለ ከተሞች 166 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተሰማርተው እያንዳንዳቸው በየዕለቱ እስከ 30 ቤቶችን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።
ባለሙያዎቹ ከቤት ለቤት አሰሳው በተጓዳኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ያከናውናሉ ብለዋል፡፡
ከገጽ ለገጽ ማስተማሪያ መንገድ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ ምን ዓይነት የጥንቃቄ እርምጃዎችን ስለመውሰድ፣ ምልክት የታየበት ሰው ሲያጋጥምም ለሚመለከታቸው አካላት እንዴት ማሳወቅ እንዳለበት የሚያብራሩ በራሪ ጽሑፎችን ይዘው በመንቀሳቀስ እንደሚያድሉም አስታውቀዋል።
በከተማዋ ከተሰማሩ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መካከል ሲስተር ሲሳይ ፈለቀ በሥራ ቀናት ብቻ ሳይሆን ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የቤት ለቤት ጉብኝቱንም በየዕለቱ በዕቅዳቸው መሠረት እንደሚያከናውኑና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግም ተገቢውን መረጃ በመሰብሰብ ሪፖርት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።