በሰቆጣ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለኮሮና መከላከል ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሰቆጣ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለኮሮና መከላከል ድጋፍ ተደረገ
ሰቆጣ ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በሰቆጣ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ የገንዘብና የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን የከተሞቹ የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይሎች ገለፁ ።
በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል አባል አቶ ገብረህይወት አዱኛ እንደገለፁት የአለም አቀፍ ህፃናት አድን ድርጅት የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ 8 ሚሊዮን ብር እገዛ አድርጓል።
ድጋፉም በኮሮና ምክንያት የመማር ማስተማር ስራ በመቋረጡ ህፃናት በቤታቸው ሆነው በሬዲዮ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያግዝ ነው።
ትምህርቱም በኽምጠኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የሚሰጡ ሲሆን ከወዲሁ የድምፅ ቀረፃው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም ተማሪዎች ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ባሉበት ቦታ ሆነው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርቱን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
የትምህርት ስርጭቱን በአጭር ጊዜ ለማስጀመር ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለራዲዮ ጣቢያው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንዲሟሉ እየተሰራ ይገኛል።
የአለም አቀፍ የህፃናት አድን ድርጅት የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ፊልድ ኦፊስ ማናጀር ምህረቱ ሞላ በበኩላቸው ድጋፉ ለትምህርት ስራና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚውል ነው።
ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ ከዞኑ የኮሮና መከላከል ከግብረ ሃይል ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከተሰጠው ድጋፍ ውስጥም አምስት ሚሊየን ብር የኮሮና ቫይረስ መከሰት ተከትሎ ከትምህርት ገበታ ውጭ ያሉ ህፃናትን ትምህርት በራዲዮ ለመስጠት የሚያስችል ነው።
ቀሪው 3 ሚሊዮን ብር ደግሞ በጤና ተቋማት እና በሰቆጣ ከተማ ለሚገኘው የለይቶ ማቆያ ማእከል የህክምና ግብዓቶችን ለማሟላት የሚውል መሆኑን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የወሎ ተወላጆች ለደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር 400 ኩንታል ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እጅጉ መላኬ ገልፀዋል ።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ 12 የወሎ ተወላጆች አንድ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው አካባቢያቸውን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
እስካሁን በተደረገ የሃብት ማሰባሰብ ስራ ከ3 ሺህ 600 ኩንታል በላይ የተለያየ የምግብ እህልና ከ24 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል፡፡
በደብረ ብርሃን የሚገኘው "ሙዳይ" በጎ አድራጎት ማህበር በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 100 ሰዎችን የአንድ ወር ቀለብ ድጋፍ ማድረጉን የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ገልፀዋል።
ድጋፉም በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ችግረኛ ሴቶች፣አረጋውያን እና ህፃናት የተሰጠ ሲሆን የዳቦ ዱቄት፣ ዘይትና ለህፃናት የሚሆን አልሚ ምግብ ያካተተ ነው።
በከተማ አስተዳደሩ የኮሮና መከላከል ግብረ ሀይል አባል ወይዘሮ እንዳዘናው ገብረፃድቅ በበኩላቸው በከተማው ለችግር የተጋለጡ 1 ሺህ 364 ሰዎች 826 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ኤልሳ ኃይለሚካኤል እንደገለፁት ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በመስተንግዶ ስራ ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው በበሽታው መከሰት ምክንያት ስራ በማቆማቸው መቸገራቸውንና ድጋፉ ጊዜያዊ ችግራቸውን እንደፈታላቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮ መንበረ ሞገስ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ድጋፉ አሁን ላይ ወረርሽኙን በቤት ውስጥ ቆይቶ ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።