በሐረሪ ክልልና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልልና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
ሐረር ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልልና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ተፅዕኖ ለችግር ለተጋለጡ አንድ ሺህ 110 አባወራና እማወራዎች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ።
በሐረሪ ክልል አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ ግምት ያላቸውን የምግብ እህልና ዘይት ለ910 አባወራና እማወራ ድጋፍ ያደረጉት የክልሉ ተወላጅና በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ በክሪ አብዱላዚዝ ናቸው።
አቶ በክሪ አብዱላዚዝ በድጋፉ ወቅት እንደተናገት በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ የሚደረገው ድጋፍና ትብብር በይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ፈጣሪ የሰጠንን ሁሉ ለወገኖቻችን የማካፈል ግዴታ አለብን ያሉት አቶ በክሪ አንድ ሰው በልቶ እያደረ ሌላው እንዲራብ የሚፈቅድ አንጀት ሊኖረን አይገባም የሚል ምክር ለግሰዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ኅብረተሰባችንን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ የምንችለው ሁላችንም እርስ በእርስ ስንረዳዳና ስንደጋገፍ ብቻ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ለጋሽ አካላት ምሥጋና አቅርበው ይህ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
በድጋፉ ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ወርዲ ሐሺም፣ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ሚስራ አብደላና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቀርሳ ወረዳ ቫይረሱ ባስከተለው ተፅዕኖ ለችግር ለተዳረጉ 200 ቤተሰቦች ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፉ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ፋሲሊቲ ጉዳይዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ አልይ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ቫይረሱ ባስከተለው ተጽዕኖ የተቸገሩ ወገኖችን እየደገፈ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም በ350 ሺህ ብር ወጪ የተገዙ የምግብ እህልና ዘይት ለ200 ወገኖች እንዲከፋፈል ተደርጓል ብለዋል።
የወረዳው ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ፀሐፊ አቶ ፋህሚ አብዲ በበኩላቸው በወረዳው ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያደረገው ድጋፍም በተለይ አቅመ ደካሞች በቤት በመቆየት ቫይረሱን እንዲከላከሉ ለሚደረገው እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።