ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን በአገር ውስጥ ማምረት ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን በአገር ውስጥ ማምረት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ በአውሮፓ ሰፊ እውቅና ካለውና ኤ ሲ ኤም ከተሰኘ የጀርመኑ የአውሮፕላን የውስጥ አካላት አምራች ኩባንያበጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ፈርሟል። የወንበር አልባሳትን፣ የደህንነት ቀበቶን፣ ምንጣፍንና ሌሎች የአውሮፕላን የውስጥ አካላት ማምረቻው ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቶ ከአራት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በተደረሰው ስምምነት መሰረት አየር መንገዱ የአውሮፕላን የውስጥ አካላቱን ምርት የሚያቀርበው ለኤ ሲ ኤም ኩባንያ መሆኑም ተገጿል። ማምረቻው ሥራ ሲጀምር ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ከመጡት የጨርቃጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ለዘርፎቹ እድገት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አስታውቀዋል። የስምምነቱ  ዓላማ በአውሮፕላን ሞተርና በሌሎች የውስጥ አካላት ጥገና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የኢትዮዽያ አየር መንገድ የጥገና አቅም ማሳደግ መሆኑንም ተናግረዋል። አየር መንገዱ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ለማምረት የሚያስችሉ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ አገሮች በማስገባት ስራውን የሚጀምር ሲሆን በሂደት ግን ጥሬ እቃዎችን ጭምር የማምረት እቅድ እንዳለው አቶ ተወልደ ገልፀዋል። በአየር መንገዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገነባው ማምረቻ ወደፊት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሸጋገርበት ሁኔታ እንዲፈጠር አየር መንገዱ እንደሚሰራ ተናግረዋል የጀርመኑ ኤ ሲ ኤም ኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አራሽ ኖሻሪ በበኩላቸው ቅድመ ስራዎች ተጠናቀው በሶስትና በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢትዮዽያ ውስጥ የአውሮፕላን የውስጥ አካላት መመረት እንደሚጀምር ተናግረዋል። የአፍሪካ አህጉርን በአየር ትራንስፖርት አንድ የማድረግ ዓላማ ይዞ ከሚሰራውና በየጊዜው እያደገ ከመጣው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ጋር መስራት ለኩባንያውና ለጀርመን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም