ቀጥታ፡

ግብፅ የሕዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል የምታደርገው ጥረት ተቀባይነት የለውም…ምሁራን

ሐዋሳ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ፍትሐዊ የውኃ ሀብት ልማቱ ተጠቃሚ ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይ የግብፅ ጫና የመፍጥር ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲሉ በሐዋሳ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

በግድቡ ጉዳይ ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ድርድር ሦስተኛ አካል ሊገባ የሚችለው ሦስቱም ሀገራት ሲስማሙ ብቻ መሆኑንም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግና ገቨርናንስ ኮሌጅ ዲን ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንደገለጹት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ክብር ማሳያ በመሆኑ ግድቡን ለማጠናቀቅ ዜጎች ከየትኛውም ዓይነት ልዩነት በመውጣት የጋራ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

የግድቡ ግንባታ የተፋሰሱን አገራት በማይጎዳ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ቢሆንም ግብፅ የጀመረችው ፕሮፓጋንዳ ትልቅ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል።

"በተፋሰሱ አገራት የውኃ አጠቃቀም ላይ በታሪክ የተፈጠረውን ወደ አንዱ ያደላ አሰራር ማረም ተገቢ ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ኢትዮጵያ ያላት በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት ዓለም አቀፋዊ ዕውነታን ያገናዘበ በመሆኑ ግብፅ አምና መቀበል እንዳለባት ተናግረዋል።

"በራስ አቅም ጀምረን አሁን ላይ የደረስንበት ደረጃ የሚያኮራና ሀገራችን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የነበራትን ጽናት ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡

ግብፅ ኢትዮጵያ ግድቡን ከተቻለ እንዳትጀምረው ካልሆነ እንዳታጠናቅቅው ባለፉት ዓመታት የተለያዩ መሰናክሎችን ስትፈጥር መቆየቷንም አስታውሰዋል።

"ኢትዮጵያውያን ይህን ችግር ማሸነፍ የምንችለው ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው አንድነታችንን ማጠናከር ስንችል ነው" ብለዋል።


ሌላው የፖለቲካል ሣይንስ ምሁር አቶ ዳያሞ ዳሌ በበኩላቸው"ግብፅ የአሜሪካውን የድርድር መድረክ በመጠቀም በአሜሪካ የቀረበውን ሀሳብ ኢትዮጵያ አልቀበልም አለች በማለት ሕግ እንደተጣሰ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ያቀረበችው ሰላም የደፈረሰ ለማስመሰል ነው" ብለዋል።

"የፀጥታው ምክር ቤት የሰላምና የፀጥታን ጉዳይ እንጂ የኢኮኖሚ ጉዳይን መመልከት አይችልም" ያሉት አቶ ዳያሞ ግብፅ የሄደችበት መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

"የግድቡ ሙሌትም በተያዘው ጊዜ ተግባራዊ መደረግ አለበት" ያሉት አቶ ዳያሞ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ሂደቱ እንዲቀጥል አስፈላጊው ጥረት መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል።

ግብፆች በዐረብ ሊግ አማካኝነት በአባይ ዙሪያ ውሳኔ ሲያሳልፉ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲታይ ለማድረግ ያለውን አማራጭም መጠቀም ይገባ እንደነበረ አስረድተዋል።

የውኃው መነሻም ሆነ የተፋሰሱ አገራት አፍሪካውያን ሆነው ሳለ አፍሪካዊ በሆነው ጉዳይ ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው አቤቱታም ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም