ቀጥታ፡

የኮቪድ 19 ን ለመከላከል የሚታጠቡ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች በመጠቀም ወጭን መቀነስ እንደሚቻል ተገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) - የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ማኅበረሰቡ የሚታጠቡ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን እንዲጠቀም ተጠይቋል።

የዓለም በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የፊት መሸፈኛ ጭምብልን ርቀት ጠብቆ መጓዝ በማይቻልበት እንደ ምግብ መሸጫ መደብርና መድኃኒት ቤት አካባቢ በተለይም ለበሽታው መተላለፊያ ዓይነተኛ ምክንያት ይሆናሉ በሚባሉት ቦታዎች መደረግ እንዳለበት ይመክራል።

ማኅበረሰቡ በተቻለ መጠን የሚታጠቡ ጭምብሎችን መጠቀም የተሻለ መሆኑንም ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታና በትራንስፖርት ላይ ኅብረተሰቡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲጠቀም አስገዳጅ መመሪያ ተላልፏል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ማኅበረሰቡ የሚታጠቡ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን መጠቀም እንዳለበት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም አድራሮ እንደሚሉትም በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታጠብ ማስክ መጠቀም የተሻለ ጠቀሜታ አለው።

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት በቀላሉ እየታጠቡ በተደጋጋሚ ለአገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ቢጠቀም የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በተለያዩ አምራች ድርጅቶች በኩል በቀላሉ በማጠብ መልሶ ለመጠቀም የሚያገለግሉ ምርቶች ለገበያ እየቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ተስፋዓለም ገለጻ እንዲህ ዓይነት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች እንደየደረጃቸው እስከ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ያገለግላሉ።

አንዳንዶች ለሕክምና ባለሙያዎች እየተባለ የሚመጣውን ሰርጅካል ፌስ ማስክና ኤን95 የሚባሉ ጭምብሎችን ይጠቀማሉ።

ከዚህ ይልቅ ኅብተረተሰቡ በቀላሉ እያጠበ የሚገለገልባቸውን ምርቶች ቢጠቀም የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።

ይህም በዋናነት ለጤና ባለሙያዎች የሚያገለግለው ጭምብል የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠርና ለአደጋ እንዳይጋለጡ ያደርጋል ብለዋል።

ለሕክምና ባለሙያዎች ተብለው የሚመረቱት በቀን ሁለት ጊዜ መቀየርን የሚጠይቁ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ደግሞ ከወጪም አንጻር ይህን ለማድረግ ስለሚቸገር ለቫይረሱ ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

ኅብረተሰቡም በቀላሉ እያጠበ የሚገለገልባቸውን ምርቶች ቢጠቀም ካልተገባ ተጨማሪ ወጭም ይድናሉ ብለዋል።

ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት፣ የመተንፈስ ችግር ያለባቸው፣ ራሳቸውን የሳቱ፣ አቅመ ደካሞችና በቀላሉ ጭምብሉን ከላያቸው ላይ ማውረድ የማይችሉ ሰዎች የፊት መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ የለባቸውም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም