አገር አቀፍ የሰላምና የመግባባት ህዝባዊ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የሰላምና የመግባባት ህዝባዊ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 አገር አቀፍ የሰላምና የመግባባት ህዝባዊ ኮንፈረንስ ሊያካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ህብረት አስታወቀ። ህብረቱ ኮንፈረንሱን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የህብረቱ ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን እንደገለፁት ህብረቱ የተመሰረተው ከ8 ወር በፊት በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በባህላዊ መንገድ ለመፍታት ነው። በዚህ መሰረት ህብረቱ የሁለቱም ክልል መሪዎችና ወገኖች በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ገልፀዋል። ይሁን እንጂ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው የሰላም እጦት በሌሎች አካባቢዎችም እየተስተዋለ በመምጣቱ የሰላም ኮንፈረንሱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ መወሰኑን ሰብሳቢው ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ መጀመሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይም በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች እንደሚካሄድ ተገልጿል። ኮንፈረንሱ የሚካሄድበት ቀን ሁሉም የቅድመ ዝግጀት ስራዎች እንደተጠናቀቁ ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። በኮንፈረንሱ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎችና የመንግስት አካላትን ጨምሮ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች ይሳተፉበታል ብለዋል። በቀጣይም በየ2 ዓመቱ አገር አቀፍ፣ በዓመቱ በሁሉም ክልሎች፣ በየ ስድስት ወሩ በሁሉም ዞኖች ለማካሄድ መታቀዱን ተናግረዋል። በወረዳ ደረጃ በቀጣይ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች በቋሚነት በባህላዊ የግጭትና አለመግባባት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም እየሰሩ የሚቀጥሉበት ዕድል ይፈጠራል ተብለዋል። ለታቀደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ የእምነት ተቋማት፣ባለሃብቶች፣የክልል መንግስታትና ሌሎች ባለደርሻ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ህብረት የበላይ ጠባቂ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ግርማ ወልደጊዎርጊስ ኮንፈረንሱ በአገር ጉዳይ በመነጋገር የዘላቂ ሰላም መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ጠቃሚ ለውጦች እየመጡ በመሆኑ ለውጡን ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በቅርቡ በኤርትራና በኢትዮጵያ በታየው የመልካም ግንኙነት ምልክት መደሰታቸውን የገለፁት የቀድሞው ፕሬዚደንት ለስኬቱ የሁለቱም አገር መንግስታትና ዜጎች በመተባበር መስራት አለባቸው ብለዋል።