ቀጥታ፡

በደሴ ኮሮናን ለመከላከል መዘናጋት እንዳይኖር ለማስተማር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማሩ

ደሴ ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ ) በደሴ ከተማ አስተዳደር በኮሮና ቫይረስ በመከላከሉ በኩል መዘናጋት እንዳይኖር ኅብረተሰቡን ለማስተማር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰማራታቸውን የአስተዳደሩ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።

የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል እንደተናገሩት  የኮሮና ቫይረስ አሁንም አሳሳቢ የጤና ሥጋት ቢሆንም በከተማው የሚስተዋለው መዘናጋት እየተባባሰ መጥቷል፡፡

የበሽታውን ገዳይነት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለኅብረተሰቡ በማድረስ ጥንቃቄ እንዲደርግና ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት ቢተላላፈም በሚፈለገው ልክ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል፡፡

ከንቲባው እንዳሉት በከተማው መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ጥንቃቄ  በመተው  ቫይረሱ የጠፋ እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ መዘናጋትና ኅብረተሰቡ ወደ ቀድሞው እንቅስቃሴ የመመለስ አዝማሚያ ታይቷበታል፡፡

የመከላከል ሥራውን በአዲስ ለመጀመርም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት 525 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡

ወጣቶቹ የተረሳውን እጅ ማስታጠብ፣ ተራርቆ መሰለፍ፤ ሰው የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ውኃና ሣሙና ማስቀመጥና አካላዊ ርቀትን ማስጠበቅ ላይ በማተኮር የመከላከያ ዘዴዎችን ያስተምራሉ ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ወጣቶችን በመደገፍና ሕግ በሚተላለፉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ራሱን አጠናክሮ በአዲስ መልኩ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ሀኒያ መሀመድ  በተለያዩ አካባቢዎች ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠርና ቫይረሱን ለመከላከል ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጻለች፡፡

በአዲስ መልኩ ወደ ሥራ ከገቡ ሁለተኛ ቀናችው ቢሆንም በተደረገው ቅንጅታዊ ሥራ ስለቫይረሱ ትምህርት የሚሰጡ ከሁለት ሺህ በላይ "ስቲከሮች"ን ታክሲዎችና ሌሎች ተሸከርካሪዎች ላይ መለጠፋቸውን ጠቅሳለች፡፡

እንደ ወጣቷ ገለጻ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎችም የእጅ መታጠቢያ ውኃና ሣሙና እያስቀመጡ ከመሆናቸውም ባለፈ ታክሲ ተራና ሰው የሚበዛባቸው ተቋሞች ላይ አካላዊ  ርቀት እንዲኖር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

በሁለት ቀናት ውስጥ ባካሄዱት የመከላከል ሥራ ኅብረተሰቡን በአዲስ መልኩ ማነቃቃትና ግንዛቤ መፍጠር እንደቻሉ የገለጸው ደግሞ ወጣት ዋሱ ሰይድ ነው፡፡

"ቫይረሱ እስኪጠፋ ድረስም ለኅብረተሰቡ ስለኮረና ግንዛቤ በመፍጠር የድርሻዬን እወጣለሁ" ብሏል፡፡

ከደሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አለባቸው ሙሄ በበኩላቸው ወጣቶች  የጀመሩት እንቅስቃሴ የተዘናጋውን ሰው  ለመመለስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ  መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ቫይረሱን ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ  የኅብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

"ቫይረሱ እየጨመረ መምጣቱ የበለጠ መጠንቀቅ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥና ችላ እንድንለው ማድረግ የለብንም" ብለዋል፡፡

በደሴ ከተማ አስተዳደር በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች  ሀብት በማሰባሰብ የመደገፍ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ግብረ ኃይሉ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም