የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል በከተማ ግብርና ቴክኖሎጂ ላይ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

187

ጎንደር፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ወጣቶችና ሴቶችን በአትክልት ልማት በማሳተፍ ጤንነታቸውን መጠበቅ የሚችሉበት የከተማ ግብርና ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ምርምር እያካሔደ መሆኑን አስታወቀ ።

በማእከሉ የውሃ አያያዝ ተመራማሪ አቶ መልኬ ደሳለኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት የምርምር ስራው ከወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የከተማ ነዋሪዎች ከንክኪና ከብክለት የጸዳ የጓሮ አትክልት በቤታቸው አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው፡፡

ቴክኖሎጂው የከተማ ነዋሪዎች በአነስተኛ ቦታ ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት አመቱን ሙሉ ቤተሰባቸውን መመገብ የሚያስችላቸው ነው ብለዋል፡፡

ወቅቱ በኮሮና በሽታ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው ለመቀመጥ የተገደዱበት ሁኔታ በመፈጠሩ ገበያ ሳይወጡ በቀላሉ የጓሮ አትክልቶችን በቤታቸው አልምተው መጠቀም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የወዳደቁ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ቆስጣ ፣ ሰላጣ ፣ ጎመንና ቲማቲምን በማልማት በአጭር ቀናት ለምግብነት ማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የቤት ውስጥ ተረፈ ምርቶችን ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት በማዘጋጀት የጓሮ አትክልቶችን በቀላሉ ማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ማእከሉ ባደረገው ምርምር ከ40 እስከ 60 ቀናት ባሉት ጊዚያት የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ለምግብነት ማዋል እንደሚቻል ማረጋጋጡን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

ማእከሉ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ በጎንደር ከተማ ቴክኖሎጂውን በማስተዋወቅ የከተማው ነዋሪዎች የጓሮ አትክልቶችን በቤታቸው በማልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ለመዘርጋት ተዘጋጅቷል፡፡

የግብርና ባለሙያዎችና የከተማው አመራሮችም በማእከሉ የተዘጋጀውን ሰርቶ ማሳያ እንዲጎበኙ በማድረግ የማስተዋወቅ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ከ80 በላይ ተመራማሪዎች ያሉት የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል በዘንድሮው አመት በግብርናው ዘርፍ ከ170 በላይ ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝ ከማእከሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም