የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመስጂድና ኢስላማዊ ማዕከል የመስሪያ ቦታ አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመስጂድና ኢስላማዊ ማዕከል የመስሪያ ቦታ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፍሪካ ህብረት አካባቢ ዓለም አቀፍ መስጂድና ኢስላማዊ ማዕከል የመስሪያ ቦታ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስረከበ።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት የተሰጠው ቦታ የህዝበ ሙስሊሙን የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሚመልስ ነው።
የመስጂድና ኢስላማዊ ማዕከል መስሪያ ቦታው የህዝበ ሙስሊሙ የኢድ በዓል ስጦታ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከቀናት በኋላ የሚከበረው የኢድ በዓል በመረዳዳት እና በመደጋገፍ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በሃይማኖትና በብሄር ከመከፋፈል በመውጣት ለአንድነትና ትብብር ትኩረት እናድርግ ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሲባል ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በየቤቱ እንዲያከብረውም ጠይቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ላልነበራቸው 71 ነባር መስጂዶችም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረክቧል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ መንግስት ላደረገው ታላቅ ስጦታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለህዝበ ሙስሊሙም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሸህ ሱልጣን አማንም ለመንግስት ምስጋና አቅርበዋል።
በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና በርካታ የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።