ቀጥታ፡

ኮይካ ለራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል 12 ሺህ ዶላር ግምት ያለው የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የኮሪያ አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) አዲስ አበባ ለራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል 12 ሺህ ዶላር ግምት ያለው የኮቪድ 19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ለሆስፒታሉ የተደረገው ድጋፍ 1 ሺህ100 የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ እያንዳንዱ 500 ሚሊ ሌትር የሆነ 750 ፈሳሽ የእጅ ሳሙና፣ 1 ሺህ የእጅ ጓንት እና 750 ሚሊ ሌትር የሆኑ ከ700 በላይ ሳኒታይዘር መሆኑ ታውቋል።

ቁሳቁሱን የተረከቡት የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰብያ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ሁንዴ ኮይካ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይም ከኮይካ ጋር በትብብር መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኮሪያ አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኪም ዶንግ ሆ ለሆስፒታሉ ድጋፉን በመስጠታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዓለም ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ማጥፋት የምንችለው በትብብር ስንሰራ በመሆኑ ድጋፍና ትብብራችን ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

ኮይካ በኮሮናቫይረስ መከላከል ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጤና ዘርፎች ለሆስፒታሉች ድጋፍና ትብብር እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮይካ ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ኢምባሲ ጋር በመተባበር  የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁስ ለኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ማድረጉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

ኮይካ በኢትዮጵያ በግብርና፣ በገጠር ልማት እና ጤና አጠባበቅ  የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም