ቀጥታ፡

በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ አገር ውስጥ ይገቡ ከነበሩ ቱሪስቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታጥቷል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012(ኢዜአ) በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ አገር ውስጥ ይገቡ ከነበሩ ቱሪስቶች 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መታጣቱን የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር አስታወቀ። 

በዚህም በዘርፉ ከሚንቀሳቀሱ ህዝበች መካከል ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለችግር ተጋልጦ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዘደንት ወይዘሮ አንድነት ፈለቀ ለኢዜአ ተናግረዋል። 

ወረርሽኙ አገር ውስጥ መግባቱ ከተረጋገጠበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም ብቻ ከ350 እስከ 400 ሺህ የሚሆኑ ቱሪስቶች በተለያየ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ይጠበቅ ነበር።

የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ በመንገደኞች ጉዞ መሰረዝና የቱሪሰት ፍሰት መቅረት ምክንያት 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መታጣቱን ወይዘሮ አንድነት ገልጸዋል።  

መንግስት በዘርፉ የደረሰውን ጫና ተከትሎ ለግሉ ሴክተር በአነስተኛ ወለድ የስራ ማስኬጃ ብድር ማመቻቸቱ ዘርፉ በተወሰነ መልኩ እንዲያገግም ይረዳልም ብለዋል።

ይሁንና ወረርሽኙ እስከመቼ እንደሚቆይ የማይታወቅ ከመሆኑ አንጻር ዘርፉ ከዚህ የባሰ እንዳይጎዳና የሚደርሰውንም ጫና ለመቀነስ ሌሎች ድጋፍ ለሚሹ ጉዳዮችም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍጹም ካሳሁን፤ በአገር ደረጃ ኮቪድ-19 በቱሪዝሙና በሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው።

በተለይም ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ በአስጎብኚ ድርጅቶች፣ በሆቴልና ሬስቶራንቶች፣ በፓርኮች፣ በሙዚየሞችና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደረና መንግስትም ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ ያደረገ ነው ብለዋል።

ለዚህም ዘርፉ የበለጠ እንዳይጎዳና እንዲያገግም ለማስቻል በመንግስት በኩል የታክስ እፎይታዎችን ከማድረግ ጀምሮ ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማገገሚያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ይህም የማገገሚያ ስትራቴጂ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተና የተለያዩ ምሁራንን ያሳተፈ ሲሆን ወደ ተግባር እየተገባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት ከ849 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተው ከ3 ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሎ እንደነበር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም