ቀጥታ፡

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎችጋር ንክኪ ሳይኖራቸው በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ሳይኖራቸው በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ  ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።  

ለአብነትም ባለፉት ሁለት ሣምንታት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ቫይረሱ የተገኘባቸው 135 ሰዎች ሲሆኑ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ  ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 230 ሰዎች መድረሱን ጠቁመዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅትም ቫይረሱ በአገሪቱ በሰባት ክልሎች፣ በሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በ40 ዞኖች መገኘቱን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል አብዛኛው በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ሁኔታ እየተቀየረ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የጉዞ ታሪክም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ሥፍራ ላይ በስፋት የመሰራጨት አዝማሚያም እየታየ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ኅብረተሰቡ ጥንቃቄውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው ከሐረሪና ከጋምቤላ ክልሎች ውጭ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ቫይረሱ መገኘቱን ገልጸዋል።

ቫይረሱንም ለመከላከል ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ከሚመለከተቻው አካላት ጋር ክትትሉ መጠናከሩን ገልጸዋል።

በተለይም በጎረቤት አገሮች የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑንና በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰበ ክፍሎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም በአማራ፣ በአፋር፣ በድሬዳዋና በሶማሌ  ክልሎች  ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ  መሆኑን ዶክተር ኤባ አስታውቀዋል።

ስለዚህም ኅብረተሰቡ የቫይረሱን መጨመርና ስርጭቱም መስፋቱን ከግምት በማስገባት የመከላከል ሥራውን እንዲያጠናክር ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

በተለይም ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች መተግበር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም