ቀጥታ፡

ሕገ መንግሥቱ ለአሁናዊ ችግሮች መፍትሔ፣ ለቀጣይ ጉዞም አመላካች በሆነ አግባብ ሊተረጎም ይገባል - የሕግ ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ሊካሄድ የነበረውን ብሄራዊ ምርጫ ለማከሄድ አቅዳ የነበረችው ኢትዮጵያ በወቅቱ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ሳቢያ ሊሰናከል ችሏል።

በወረርሽኙ ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ ከ50 በላይ አገሮች ዘንድሮ የነበራቸውን የምርጫ መርሃ ግብር ሰርዘዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፊታችን ነሐሴ ምርጫውን ለማካሄድ ከወራት በፊት ቢያሳውቅም፤ በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫውን ማከናወን እንዳልቻለ ከሳምንታት በፊት አሳውቋል። 

ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከዳኝነት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ ከዩኒቨርሲቲ አስተማሪነትና እስከ ግል ጥብቅና በሕግ ዘርፍ ልምድ ያካበቱ አንጋፋው ምሁር አቶ ታምሩ ወንድማገኝ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም ሕገ መንግስት የሰፋ፣ የከበደ ሃላፊነት፣ የህዝቡን ቀጣይ እጣ ፈንታና ዕድገት የሚወስን ሰነድ ቢሆንም ችግሮች ሲያጋጥሙ በየወቅቱ እንደሚታረም በሌሎች አገሮችም የተለመደ እንደሆነ የአሜሪካን ሕገ መንግስት በማንሳት ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ፍስሐፂዮን መንግስቱ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ከገንዘብ ሚኒስትር አማካሪነት ጀምሮ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ዩኒቨርሲቲዎች በአስተማሪነትና አማካሪነት ላለፉት 50 ዓመታት ያገለገሉ የምጣኔ ሐብትና የሕግ ምሁር ናቸው።

ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት ካለምርጫና ሕገ መንግስት መቆየቷን ገልጸው፤ የህብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግር የምርጫ ሳይሆን የዳቦ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እንደሆነ ያምናሉ።

በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበትና አገሪቱም በኮቪድ-19 ወረረሽኝ ቀውስ ባጋጠማት ጊዜ ምርጫ ማካሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን ያስረዳሉ።

''የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከብርና አገራዊ ቀውስ ሲያጋጥም ችግሩን ለማለፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚደነገግ በሕገ መንግስቱ አንቀዕ 93 የተመላከተ ጉዳይ ነው'' ይላሉ አቶ ታምሩ።

በዚህ ጊዜም ምርጫ ሳያደርጉ ማለፍ በሌሎች አገሮች ዘንድም የነበረ ተሞክሮ እንደሆነ እንግሊዝ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለ10 ዓመታት ምርጫ ሳታካሂድ መቆየቷን ለአብነት ያስታውሳሉ።

አገራዊ ቀውስ በሚፈጠርበት ጊዜም በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት የስልጣን ጊዜ ማራዘም ፖለቲካ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ እንደሆነ ገልጸው፤ ሕገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ አግባብ መተርጎም እንደሚገባው ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም አገራዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ መቼ፣ በማን፣ እንዴት በምን መልኩ መተርጎም እንዳለበት በሕገ መንግስቱ የተቀመጠ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

በዚህም አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ብትገባ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃላፊነት እንጂ የሌሎች ፖለቲከኞች እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ፍስሐፂዮን ገለፃ 'ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም' በማለት ክርክር የሚያነሱ ሰዎች ሃሳብ ተቀባይነት የለውም።

''ዋናው ምርጫ ሳይሆን እምነትና መተማመን፣ ንግግርና ስራ የሚያጣጣሙ መሪዎች አገር ላይ ሲኖሩ ነው'' ይላሉ።

በርካታ ፖለቲከኞች ከስልጣን ሽኩቻ ይልቅ የአገር አንድነትና የህዝብ ጥቅምን ማስቀደም እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

ያም ሆነ ይሕ ምሁራኑ ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜው ትኩረት ጥንቃቄ የሚያሻው ስለመሆኑ ይስማማሉ።

ሕገ መንግስታዊ ትርጉም በርካታ ሃላፊነት ያለበት፣ ማማከር የሚጠይቅ፣ አሁናዊ ችግሮችን አገናዝቦ መፍትሔ የሚያፈልቅ፣ ለነገም ቀጣይ መንገድ የሚያመላክት በሆነ አግባብ መተርጎም እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ትርጉም ለመስጠት የተመረጡ ግለሰቦች እውቀታቸው ታይቶ፣ በጉዳዩ ላይ ጥናታቸው ተፈትሾ፣ አስተሳሰባቸውም ከወገንተኝነት ነጻ ስለመሆኑ ተረጋገጦ መሆን አለበት ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም