ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች በብዛት የሚገኙት በሁለት ክፍለ ከተሞች ነው... ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) በከተማዋ ልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በቫይረሱ የተጠቁ በርካታ ሰዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ አስታወቁ ።

ሠርግና ለቅሶ ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት አስተዋጽዖ አድርጓል ተብሏል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከተያዙት 365 ሰዎች መካከል 63 በመቶ  ወይም 228 ሰዎች በከተማዋ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቫይረሱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች መገኘቱን ገልጸው፤ የቫይረሱ ስርጭት በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በከተማዋ በቫይረሱ ከተያዙ አጠቃላይ 228 ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በልደታ ክፍለ ከተማ ይገኛሉ ብለዋል።

በአጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች 56 ሰዎች ወይም 16 በመቶ የሚሆኑት የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደሌላቸው ዶክተር ኤባ ተናግረዋል።

ከነዚህም 48 በመቶ የሚሆኑት አዲስ አበባ እንደሚገኙና ከነዚህም 93 በመቶው በልደታና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ለአብነትም ከሰሞኑ በልደታ በተደረገው በአንድ አዛውንት ላይ በተገኘው የኮሮና ቫይረስ 67 ሰዎች ንክኪ ያላቸው ሰዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

በእኚህ አዛውንት ምከንያትም አራት የቅርብ ሰዎችና አንድ ጎረቤት መጠቃታቸውን ጠቁመዋል።

ከአዛውንቱ ጋር ንክኪ  ያላቸውንም 95 ሰዎች ምርመራ በማድረግ 27 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በዚሁ ልደታ ክፍለ ከተማ በአንድ ጊዜያዊ ማረሚያ ቤት በድምሩ 66 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ተረጋግጧል ብለዋል።

ይህም ታራሚዎችንና ሌሎች አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን እንደሚያጠቃልል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ይህም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በድንገተኛ በተደረገ የናሙና ምርመራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመቀጠልም አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመዲናዋ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት የሚታይበት ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ከባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚገባም ዶክተር ኤባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ሰርግና ለቅሶ ለቫይረሱ ስርጭት ዋነኛ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ እንዲህ ያሉ ማኅበራዊ ክንውኖችን ማስቀረት እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም