ቀጥታ፡

ኩባንያው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) የ"ሞኤንኮ "ኩባንያ ሀዋሳ ቅርንጫፍ ኮሮናን ለመከላከል እንዲረዳ 300 ሺህ ብር በሆነ ወጪ የገዛውን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የኩባንያው ቴክኒካል ሰርቪስ ማኔጀር አቶ ሰለሞን በሽር ድጋፉን ትናንት ለደቡብ ክልል ጤና ቢሮ  አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት አቶ ሰለሞን እንደገለጹት ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ 35 ካርቶን ሳኒታይዘርና 240 ካርቶን ሳሙና ማበርከቱን ገልጸዋል።

ደጋፉ የኮሮና ወረርሽኝን  ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

አዲስ አበባ የሚገኘው ዋናው መስሪያ ቤታቸውም በቅርቡ አራት ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ሁለት አንቡላንሶችን በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ  ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ አቅናው ካውዛ  በበኩላቸው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሞኤንኮ ያደረገው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

"ህይወት አድን ስራ በአንድ ሴክተር ብቻ የሚሞከር አይደለም፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ስራ ለማጠናከር ኩባንያው ድጋፍ ማድረጉ አስተማሪ ተግባር ነው "ብለዋል።

ወረርሽኙን ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ያሉት የጤና ባለሙያዎች ስለሆኑ ዛሬም ጤና ተቋሞች የንጽህና መጠበቂያ ስለሚያስፈልጋቸው  ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ካሁን በፊትም ኩባንያው የጤና ቢሮው አምቡላንሶችን ጨምሮ ሌሎችንም ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ሰጥቶ በመጠገን ሲደግፋቸው መቆየቱንም አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ከተቋቋመ 61 ዓመታትን ያስቆጠረው "ሞኤንኮ" ከ20 በላይ የተሽከርካሪ "ብራንዶችን" የሚያስመጣና  በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች  ቅርንጫፎች ያሉት መሆኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም