ቀጥታ፡

ተመድ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በአባይ ግድብ ፕሮጀክት ሥምምነት ላይ እንዲደርሱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12/2012 (ኢዜአ) ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ሥምምነት ላይ ለማድረስ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚያበረታቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ አስታወቁ ።

በሦስቱ ሀገሮች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በሚደረገው ድርድር ላይ የተሻለ መሻሻል እየተደረገ እንደሚገኝ የዋና ፀሐፊው ቃል አቀባይ ትናንት ማስታወቃቸው ተመላክቷል።

ዋና ፀሃፊው እ.ኤ.አ. የ2015 በታላቁ የህዳሴ ግድብ የልማት መርሆዎች፣ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ትብብርን የሚያጎላ፣ ለጋራ ጥቅም ፣ ለመልካም እምነት ፣ ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግና የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች አስፈላጊነት ላይ በማተኮር አጽንኦት እንደሰጡት ቃል አቀባዩ መናገራቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ድረ ገጽ አስነብቧል።

ዋና ጸሃፊው በነዚህ መርሆዎች መሠረት መልካም ወደሆነ ሥምምነት እንዲመጡ እንደሚያበረታቱ ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ73 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር መገለፁም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም