ኮቪድ-19 በየመን የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19 በየመን የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በየመን የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያደርገውን ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክር ተጠየቀ።
በኢትዮጵያ የየመን አምባሳደር ያህያ አል-ኢርያኒ በስዕል ጥበበኞች የተሰራ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ምስል ለሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ አስረክበዋል።
ስዕሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ የየመን ማኅበረሰብ አባላትና ኤምባሲው ኢትዮጵያ ለየመን ስደተኞች ለምታደርገው አቀባበል፣ ለምትሰጠው መጠለያና ድጋፍ ምስጋና ለማቅረብ የተበረከተ መሆኑ ተገልጿል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ፈልሰን አብዱላሂ ከየመን የተበረከተው ስጦታ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የታዩ ለውጦች አበረታች ለመሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያና የመን ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸውና በባህል፣ በታሪክ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በዲፕሎማሲ የጠበቀ ትስስር በመመሰረት ለጋራ ተጠቃሚነት ሲሰሩም ቆይተዋል።
የመን ካለችበት ሁኔታ ፈጥና እንድትወጣና ወደ ቀደመ ሠላሟ እንድትመለስ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ጽኑ ፍላጎት መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ዓለምን እየፈተነ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በየመን የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
መርሃ ግብሩን ላስተባበረው በኢትዮጵያ የየመን ኤምባሲና ስጦታውን ላዘጋጁት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችም ምስጋና አቅርበዋል።