ኢንተርፕራይዙ 'ከመስሪያ ቦታ እንድለቅ ተደርጌያለሁ' በሚል ላቀረበው ቅሬታ በመመሪያው መሰረት ውሳኔ ማሳለፉን ክፍለ ከተማው ምላሽ ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዙ 'ከመስሪያ ቦታ እንድለቅ ተደርጌያለሁ' በሚል ላቀረበው ቅሬታ በመመሪያው መሰረት ውሳኔ ማሳለፉን ክፍለ ከተማው ምላሽ ሰጥቷል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2010 ኢንተርፕራይዙ 'ከመስሪያ ቦታ እንድለቅ ተደርጌያለሁ' በሚል ላቀረበው ቅሬታ በመመሪያው መሰረት ውሳኔ እንዳሳለፈ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ምላሽ ሰጥቷል። ቅሬታ አቅራቢው ወጣት ወንድይራድ አስማማው በ1996 ዓ.ም በ2ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በግል ኢንተርፕራይዝ በመደራጀት በብረታ ብረት ዘርፍ ተሰማርቶ ሲሰራ መቆየቱን ይናገራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን 2006 ዓ.ም በስራው ላይ ዕድገት በማምጣት በሰባት ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሸጋገር በተለምዶ አለም ባንክ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ለቤቶች ግንባታ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ያመርታል። ዩኒኬም ፕላስቲክ በተሰኘ የኢንተርፕራይዝ ስያሜ ለቤቶች ግንባታ የሚያገለግሉ ከ16 ዓይነት በላይ የፕላስቲክ ምርቶችን በማምረት ለቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ያቀርባል። "ለ32 ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር በዘለለ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሬን ከማዳን አንፃር የበኩሌን አስተዋፆ እያበረከትኩ ነው" የሚለው ይህ ወጣት አሁን ላይ ካፒታሉ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ይናገራል። ይሁንና ወጣት ወንድራድ መንግስት የማምረቻ ቦታ ቃሊቲ አካባቢ በታህሳስ የሰጠው ቢሆንም ክፍለ ከተማው መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ 'ከአምስት ዓመት በላይ ሆኖሀል' በሚል ከመስሪያ ቦታው ሊያስነሳው በመሆኑ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ተናግሯል። የተሰጠው ቦታ የግንባታ ፈቃድ፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማና ሌሎች ጉዳዮች የሚቀሩ በመሆናቸውና የፋብሪካው ግንባታም ሳይከናወን ክፍለ ከተማው ቦታውን እንዲለቅ መደረጉን ገልጿል። በተጨማሪም በፋብሪካው ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መሳሪያዎች ከአዲስ ካፒታል በብድር የተገኙ በመሆናቸው ፋብሪካው ቢዘጋ እንኳ መስራት ሲያቆሙ ለብልሽት ይዳረጋሉ የሚል ስጋት አድሮበታል። ወጣት ወንድይራድ አሁን እያመረተበት ያለበት ቦታ ጠባብ በመሆኑ ተጨማሪ የግለሰብ ቤት ተከራይቶ ለመስራት መገደዱን ጭምር ተናግሯል። ክፍለ ከተማው ለሌሎች የተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች ቦታውን ፈልጌዋለው ይበል እንጂ በአካባቢው አዲስ የተሰሩና ከ3ዓመታት በላይ ተዘግተው የተቀመጡ የመስሪያ ሼዶች መኖራቸውንም ወጣት ወንድራድ ገልጿል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ለዘገባ በስፍራው ባቀናበት ወቅት በርካታ ነባር የተዘጉ ሼዶችና አዲስ የተገነቡ ሼዶችን ያለ ሥራ ዝግ ሆነው ተመልክቷል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በበኩሉ የመስሪያ ቦታዎች የማምረቻ፣ ማሣያና መሸጫ ማዕከላት አስተዳደር፤ አሰጣጥና አጠቃቀም መመሪያ ከሚፈቅደው ውጪ ከአምስት ዓመት በላይ በቦታው ላይ በመቆየቱ ለሌሎች የተደራጁ ወጣቶች ቦታውን አስለቅቆ ለመስጠት መሆኑን ገልጿል። በክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ጥቃቅንና አነስተኛ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ኩታ፤ 5 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውና ሀብት ያፈሩ ኢንተርፕራይዞች በመመሪያው መሰረት እንዲለቁ ከክፍለ ከተማው በመጣ ትዕዛዝ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ይናገራሉ። በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 የመስሪያ ቦታዎች አስተዳደር ንዑስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሌክሳንደር ዝናቡ፤ የመስሪያ ቦታዎች መመሪያ የሚፈቅደው እስከ አምስት ዓመት ድረስ በመሆኑ ኢንተርፕራይዙ እንዲለቅ መወሰኑን ተናግረዋል። የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተደደር ኤጀንሲ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቆያ ላሌ፤ ማንኛውም ኢንተርፕራይዝ በመስሪያ ቦታው መቆየት የሚችለው ጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ እስኪደርስ ድርስ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል። 'ጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ይሸጋገራል' ያሉት ኃላፊው ወደ ታዳጊ መካከለኛ ከተሸጋገረ ደግሞ ከኤጀንሲው የድጋፍ ማዕቀፍ እንደሚወጣ ነው የገለፁት። በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ ቦታውን ለቆ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው የገለፁት። ቀድሞ ተሰርተው ከሶስት ዓመት በላይ ዝግ ሆነው የቆዩ እና አዳዲስ ተሰርተው ያልተላለፉ ሼዶችን ለምን ያደራጃችኋቸወን ወጣቶች ሳታስገቡ እየሰራ ያለን ኢንተርፕራይዝ ለማስወጣት ፈለጋችሁ? ሲል ኢዜአ ጠይቋል። አቶ መቆያ ምላሽ ሲሰጡ፤ የተዘጉ ሼዶች በግብረ ኃይል ተከፍተው፣ አዳዲሶቹም ተካተው ለተደራጁ ወጣቶች ተላልፈው ወጣቶቹ የንግድ ፍቃድ፣ የብድርና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች እየፈፀሙ ስለመሆኑ ተናግረዋል። የማምረቻ ማሣያና መሸጫ ማዕከላት አስተዳደር፤ አሰጣጥና አጠቃቀም መመሪያ ቁጥር 1/2006 ኢንተርፕራይዞቹ በማዕከላቱ የሚቆዩት መሰረተ ልማት ተሟልቶ ውል ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የሚታሰብ እስከ አምስት ዓመት ይሆናል ይላል። አምስት ዓመት ሳይሞላው ወደ ታዳጊ መካከለኛ ለመሸጋገር አቅም የፈጠረ ኢንተርኘራይዝ በፈለገበት ዓመት ሊሸጋገር እንደሚችልም እንዲሁ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህዳር 14 ቀን 2010 ዓ ም ለአስሩም ክፍለ ከተማ በላከው ደብዳቤ አዳዲስ የስራ ፈላጊዎችን የቦታ ችግር ለመፍታት ሲባል ከአንደኛ ዙር እስከ ሶስተኛ ዙር ያሉ ተመራቂ ኢንተርፕራይዞች ከመስሪያ ቦታቸው እንዲለቁ ውሳኔ አስተላልፏል።