ቀጥታ፡

በጅማ ከተማ አዋጁን የተላለፉ 27 ግለሰቦች በገንዘብ ተቀጡ

ጅማ ግንቦት 11/2012 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌን ተላልፈው ተገኝተዋል የተባሉ 27 ግለሰቦች በገንዘብ መቀጣታቸውን የከተማዋ ኮሮና መከላከል ገብረ-ኃይል አስታወቀ።

የግብረ -ኃይሉ አባል የሆነው የከተማዋ  ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ዲቪዚዮን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አውግቸው እንደገለጹት ከተቀጡት ግለሰቦች መካከል 18ቱ ድንጋጌውን ተላልፈው በከተማው የእምነት ተቋማት አካባቢ ተሰባስበው የተገኙ ናቸው።

የእነዚህን ግለሰቦችን ጉዳይ ፖሊስ አጣርቶ መዝገባቸውን ለጅማ ከተማ አቃቤ ህግ በማስተላለፍ የተመሰረተባቸውን ክስ የተመለከተው የከተማዋ  ወረዳ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው ከ700 ብር እስከ 1000 ብር እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንቦት 9/2012 ሌሊቱ ስድስት ሰዓት አካባቢ በሂርማታ መንቲና ቀበሌ ዘጠኝ ሰዎች በጠባብ ቤት ውስጥ ተሰባስበው ሺሻ ሲያጨሱ እንደተደረሰባቸው  ዋና ኢንስፔክተር ገዛኸኝ አመልክተዋል፡፡

በዚህም የአዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ ተሰባስበው ሺሻ በማጨስ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የወረዳው ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው  በ500 ብር እንዲቀጡ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም