ቀጥታ፡

የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁች ደገፈ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል ግምታቸው ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የተለያዩ ቁሳቁችን ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ኮቪድ-19 ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ የድርሻዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ተገልጿል።


የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት በሶስት ዙር ከ5 ሚሊዮን 269 ሺህ 841 ብር ግምት ያላቸውን ቁሳቁሶችን በድጋፍ አበርክቷል።

ዛሬ በድርጅቱ ውስጥ በተካሄደ የድጋፍ አሰጣጥ ስነ ስርዓት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የፌዴራል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ተገኝተዋል።

ድጋፉ ለክልሎችና በአዲስ አበባ ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በድርጅቱ ቅርንጫፎች አማካይነት እንደሚከፋፈል የድርጅቱ የፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘመዴ አበበ ተናግረዋል።

የዛሬው ድጋፍ በኦሮሚያና ለሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰራጭ ታውቋል።

በድጋፉ የጋራ መገልገያ ቁሳቁሶችም መካተቱም ተገልጿል።

ትልልቅ የውሃ ታንከሮችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ለመስራት የሚያገለግሉ ድምጽ ማጉያዎች ለጋራ መገልገያነት የተበረከተ ሲሆን ሳኒታይዘር፣ ሳሙና፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማክስና ምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለተለዩ ሰዎች የሚሰራጭ እንደሆነ ተገልጿል።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በሁለት ዙሮች በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ለ40 የጤና ተቋማት የህክምና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግና በተለያዩ ልማት ስራዎች እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ ጸሎት በማድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስም ቤተክርስቲያኗ የጀመረችንውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡም በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር እንዲቻል ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት የሚሰጠውን ምክር በመቀበል እንዲተገብር አሳስበዋል።

የፌዴራል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማህበራት አበረታች ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ አባላት በሽታውን ለመከላከል ሲባል ፕሮጀክቶችን ጭምር በማጠፍ እየሰሩት ላለው ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም