በአጎለላ ጠራ ወረዳ ለተቸገሩ አንድ ሺህ 600 የቤተሰብ አባላት የምግብ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአጎለላ ጠራ ወረዳ ለተቸገሩ አንድ ሺህ 600 የቤተሰብ አባላት የምግብ ድጋፍ ተደረገ
ደብረብርሃን ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ) በሰሜን ሸዋ ዞን አጎለላ ጠራ ወረዳ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ አንድ ሺህ 600 የቤተሰብ አባላት የምግብ ድጋፍ መደረጉን የወረዳው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ዮርዳኖስ ተከስተ እንደገለጹት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ምክንያት ያጋጣማቸውን ችግር ለማቃለል እየተሰራ ነው።
በዚህም በወረዳው ከሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ሌሎች በጎ አድራጊዎች ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከተሰበሰበው ሀብት ውስጥም በ741 አባወራዎች ሥር ለሚተዳደሩ አንድ ሺህ 600 የቤተሰብ አባላት በነፍስ ወከፍ አስር ኪሎግራም ዱቄት፣ አንድ ሊትር ዘይትና ሁለት ሊትር ፈሳሽ ሣሙና ተገዝቶ ዛሬ መከፋፈሉን አስታውቀዋል።
ድጋፍ ካደረጉት መካከልም ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመው ይኸው ድርጅቱ ተጨማሪ በጀት መድቦ ቫይረሱን ለመከላከል በማገዝ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ውስጥ የጫጫ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቀለም ደምሴ እንዳሉት ባሕላዊ የስፌት ዕቃዎችን ሰርተው ለገበያ በማቅረብ ኑሮቸውን ይመሩ ነበር።
ወረርሽኙ ከመጣ ወዲህ የሰዎች እንቅስቃሴ በመገደቡ ለስፌት የሚሆነውን ጥሬ ዕቃና ገዥ በማጣታቸው ለችግር ተጋልጠው ቢቆዩም ዛሬ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ማሩ በበኩላቸው የተደረገላቸው ድጋፍ የራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ችግር ለማቃለል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።