የዱብቲና አካባቢው ተወላጆች ማህበር ከ100 በላይ ለመሆኑ አቅመ-ደካሞች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የዱብቲና አካባቢው ተወላጆች ማህበር ከ100 በላይ ለመሆኑ አቅመ-ደካሞች ድጋፍ አደረገ
ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የዱብቲ አካባቢ ተወላጆች ማህበር አባላት ከ100 በላይ ለሚሆኑ አቅመ-ደካሞች የምግብ ድጋፍ አደረጉ።
አባላቱ የምግብ ድጋፉን ያደረጉት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ያሰባሰቡት ከ209ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ሲሆን በዱብቲ ከተማ ለሚገኙ አቅመ-ደካሞች እንዲከፋፈላቸውም አድርገዋል።
የማህበሩ ተወካይ ወይዘሮ ዘይባ ዩሱፍ ትናንት ድጋፉን ለተጠቃሚዎች በተከፋፈለበት ወቅት እንደተናገሩት ከተቋቋመ ዓመታት የሆነው ማህበራቸው በዱብቲና አካባቢ ለሚካሄድ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በመንግስት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በአዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የዱብቲ ተወላጆች ማህበራዊ ሚዲያን ተጥቅመው በአጭር ጊዜ ባሰባሰበው ገንዘብ ለ104 ሰዎች የምግብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከድጋፉ መካከል የምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታ እና ማካሮኒ ይገኙበታል።
በቀጣይም የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታዘርና በድጋፍ ያገኙትን አራት የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል
የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ተወካይ ወይዘሮ መዲና መሐሙድ በበኩላቸው ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኘ ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር የዱብቲ ተወላጅ ማህበር አባላት ካላቸው ውስን ገቢ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ለወገናቸው ለመድረስ ያደረጉት ድጋፍ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።
የዲብቲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አወል ሀሰን በበኩላቸው ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ከተማ አስተዳደሩ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር አቅመ-ደካሞችን ለመደገፍ ጥረት እታደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ላይ የራስ አገዝ ማህበራት ተሳትፎ የማይናቅ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
"በአዲስ አበባ የሚኖሩ የዱብቲ አከባቢ ተወላጆች ማህበር በጎ አድራጎት ለሌሎችም አርአያነት ያለው አስተማሪ ተግባር ነው" ብለዋል
ድጋፍ ከተደረጋላቸው መካከል ወይዘሮ ሉባባ ዳውድ በሰጡት አስተያየት ባለቤታቸው የአካል ጉዳተኛና ስራም የሌላቸው በመሆኑ ኑሮቸውን እንጀራ በመሸጥ እንደሚመሩ ተናግረዋል።
ማህበሩ ያደረገላቸው ድጋፍ ያላሰቡትና በዚህም መደሰታቸውን ገልጸዋል።