በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ ተያዘ

አዳማ ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ)  ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮንትሮባንድ ዕቃው ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሃንጫር ወረዳ ወደ አዳማ ሲጓጓዝ የነበረ ነው።

በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አአ 69486 አይሱዙ የጭነት መኪና ሲጓጓዝ የነበረው  የኮንትሮባንድ  ዕቃ 71 ሺህ 500 ስቴካ ሲጋራ ነው ተብሏል።

በሕገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረው ሲጋራ ትናንት ማታ በፈንታሌ ወረዳ መርቲ ቀበሌ  በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ሲደርስ በፌዴራልና በአካባቢው ፖሊስ አባላት  ቅንጅት መያዙን ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ኮንትሮባንድ ጭኖ የተገኘው ተሽከርካሪ ሾፌርና ረዳቱ በቁጥጥር ሥር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ጨምረው ገልጸዋል።

ሲጋራውን ደብቀው ለማሳለፍ 24 ኩንታል ሰሊጥና አምስት ኩንታል ከሰል ከላይ ደርበው በመጫን ለማጭበርበር የሞከሩ ቢሆንም በኅብረተሰቡ ትብብርና ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ መያዙን ገልጸዋል።

የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚና በጤናም ጭምር ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የመከላከል ሥራውን እንዲያጠናክር ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም