ማህበሩ ከ450 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ ለአካል ጉዳተኞች አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከ450 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ ለአካል ጉዳተኞች አደረገ
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ለደረሰባቸው አካል ጉዳተኞች ከ450 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያደረገው ከ700 ለሚበልጡ አካል ጉዳተኞች መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አቶ ተሰማ ሰብስቤ ገልጸዋል።
ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ ለሆኑ በአዲስ አበባና በክልሎች
ለሚኖሩ አካል ጉዳተኞች እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል።
ድጋፉ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አቅም ካላቸው አካል ጉዳተኞችና ከማህበሩ ቋት መሰባሰቡን አስረድተዋል።
ከአሁን በፊት ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም፤ በአገሪቷ ካለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
በመሆኑም አቅም ያላቸው ወገኖችና የሚመለከታቸው አካላት ወረርሽኙ እስኪያበቃ ድጋፉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በተለይ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች ለንክኪ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ልገሳ መጠናከር አለበት ብለዋል።
ድጋፉን ካገኙት መካከል ወይዘሪት መሠረት ተክለማርያም "ተንቀሳቅሶ ለመስራት አመቺ ባልሆነበት በዚህ ወቅት ለአካል ጉዳተኞች የተደረገው ድጋፍ አስደስቶኛል" ብላለች።
በኢትዮጵያ ኮቪድ 19 የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል ወገን ወገኑን የሚረዳባቸው መርሐ ግብሮች እየተካሄዱ ናቸው።
በተቋማትና በግለሰቦች አነሳሽነት የሚካሄዱት መርሐ ግብሮች በአብዛኛው የምግብና የንጽህና መጠበቂያዎችን መስጠት ያካትታሉ።