ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

ሠመራ ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ የቫይረሱ መከላከል ግብረ-ኃይል ገለጸ።

የግብረ- ኃይሉ አባልና የክልሉ  ጤና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ እንደገለጹት በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ከመደበኛ የጤና አገልግሎቶች በተጓዳኝ በክልሉ የተለያዩ የቅድመ -መከላከል ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል።

ከዚህም ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በጋላፊ በኩል የሚገቡ ከባድ የመኪና አሸከርካሪዎች የሙቀት ልኬት በማድረግ የጥንቃቄ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በክልሉ 26 ወረዳዎች የተጀመረው የቤት ለቤት ምርመራ እስካሁን ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ክልሉ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ኅብረተሰቡን ከቫይረሱ ለመታደግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ዕቅድ በማዘጋጀት የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ያሲን ተናግረዋል።

በተለይም ክልሉ ከጅቡቲ ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋራ፣ ዋና የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ መስመር አቋርጦት የሚያልፍበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ተጋላጭነት ለመቆጣጠር  ጥረት እየተደረገ ነው።

በሁሉም ወረዳዎች የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ከማዘጋጀት ሌላ በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሕክምና ማዕከሎችን በማደራጀት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የአስተምህሮ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም በተለይም አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በኩል የሚፈለገውን ያህል ለውጥ በኅብረተሰቡ ዘንድ አይታይም ብለዋል።

የጤና ቢሮው  ምክትል ኃላፊ እንዳሉት ይህንን ክፍተት ለማስተካከል የክልሉ ከፍተኛ አመራሮ እስከታችኛው የአስተዳዳር እርከን ድረስ ወርደው የሕዝብ ንቅናቄና ተጋላጭነትን የሚቀንሱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በቫይረሱ መከላከል ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰጡ የሎግያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ኡስታዝ ዓሊ አብዱ በየጊዜው የጤና ባለሙዎችም ሆኑ መንግሥት ስለቫይረሱ መከላከያ መንገዶች የተለያዩ መረጃዎች እያስተላለፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም አሁንም በኅብረተሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመሆኑ የማስተማሩ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

አሽከርካሪ የሆነው የእዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ያሲን መሀመድ በበኩሉ በሚሰጠው አገልግሎት መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች አክብሮ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ከኅብረተሰቡ የሚስተዋለው መዘናጋት መታረም እንዳለበትም አመልክቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም