ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህርዳር ግንቦት 10/2012 የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ በተሸጋገረበት ወቅት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የአማራ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ላቀ ጥላዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅ የአገራችን ሉአላዊነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ጉዳይ ነው።
መንግስትና ህዝብ በራሳቸው ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሌት ከቀን በመስራታቸው ግድቡ ውሃ መሙላት በሚጀምርተበት ደረጃ ማድረስ እንደተቻለ ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ህዝብም በቦንድ ግዥና ሌሎች የሃብት ማሰባሰቢያ መንገዶች እስከ አሁን ከ1ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ለግድቡ ግንባታ ጥቅም ላይ እንዲውል አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚሆነው ገንዘብ የተሰበሰበው የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት በዚህ ዓመት መሆኑ ህዝቡ የግድቡን ግንባታ የህልውና ማረጋገጫ ጉዳይ አድርጎ ለመውሰዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በቦንድ ግዥም የክልሉ ባለሃበት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የመንግስት ሰራተኛውና ሌላው ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ማድረጉን ሃላፊው አስታውቀዋል።
ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ከመጣው የኢኮኖሚ መዳከም አንጻር መንግስት በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ገንዘብ ለመሰብሰብ ባይችልም ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያደረገው ድጋፍ ግን የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ግድቡ በደለል እንዳይሞላና ረጅም አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በአፈርና ውሃ እቀባ ስራ 24 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግምት ያለው የጉልበትና የእውቀት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ 73 በመቶ እንዲደርስ የክልሉ ህዝብ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ጠቁመው "አሁን ላይ ወደ ድል ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ በአንድነት ጸንቶ መቆምን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ መላው ህዝብ የጋራ አስተሳሰብና አመለካከት መያዙ ግንባታውን ለማደናቀፍ የተሰለፉትን ኃይሎች ሴራ የሚያመክን ነው ብለዋል።
በመንግስት ስራ የሚተዳደሩት አቶ ደሳለኝ ካሴ በሰጡት አስተያየት የህዳሴው ግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ ቃል በገቡት መሰረት ለተከታታይ አምስት ዓመታት ቦንድ መግዛታቸውን ተናገረዋል።
በዚህም ከዘጠኝ ሺህ ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውን አውስተው አሁን ላይ የውሃ መያዝ ወደ ሚጀምርበት ምእራፍ መሸጋገሩ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው ፍጆታ ቀንሰው ቦንድ በመግዛት አሻራቸውን ያሳራፉበት ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስም በገንዘብ፣ በእውቀትም ሆነ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ጭምር ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
ሌላዋ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት በየነ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ በሙሉ አቅማቸው ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሚዲያ እንደምንሰማው የታችኞቹ አገራት የሚያካሂዱት የሴራ ዘመቻ ለመመከትም ሁሉም የአገራችን ህዝብ በጋራ መቆም አለበት ብለዋል።