ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 35 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 1775 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 35 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

በዚህም እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 352 ደርሷል።

የጤና ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው እድሜያቸው ከ18 እስከ 80 ዓመት የሆኑ 17 ወንድና 18 ሴት ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተለዩት 29 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል (ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ) ፣ 4 ሰው ከሶማሌ ክልል ጂግጅጋ ለይቶ ማቆያ እንዲሁም 1 ሰው ከአማራ ክልል አጣየ ለይቶ ማቆያ መሆናቸው ታውቋል።

ከነዚህ መካከልም 6ቱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 24 በበሽታው ከተያዘው ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸውና 5 ሰዎች ደግሞ የወጭ ሀገር ጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክክ እንደሌላቸው ዶክተር ሊያ በፌስቡክ ገጻቸው ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ ሰዎች 229 ናቸው።
ተጨማሪ 3 ሰው ያገገመ ሲሆን እስካሁን 116 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት የ5 ሰዎች ህይወት አልፏል።

እስካሁን አጠቃላይ 59, 029 የላቦራቶሪ ምርመራ መከናወኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ህብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገበር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም