ቀጥታ፡

በአባይ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የተፈረሙ ውሎችን ኢትዮጵያ ውድቅ ስታደርግ ኖራለች... ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) በአባይ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የተፈረሙ ውሎችን ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረግ የጀመረችው አሁን አለመሆኑንና በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መሪዎች መካከል የተፈረመው ''የመርህ ስምምነትም'' ግልጽና አሻሚ ትርጉም የሌለው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ግብጽና ሱዳን የአባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም የተለያዩ ስምምነቶችን መፈራረም የጀመሩት ከቅኝ ግዛት ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል።

የስምምነቶቹ ዋነኛ ዓላማም አገራቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኞቹን የተፋሰስ አገሮች በማግለል ውሃውን ፍትሃዊነት በጎደለው መልኩ በብቸኝነት መጠቀም መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የቀደሙት ስምምነቶች በወቅቱ ቅኝ ገዥዎች የነበሩት ታላቋ ብሪታኒያና ጣሊያን የላይኞቹን ተፋሰስ አገራት ባገለለ መልኩ የግብጽና ሱዳንን ጥቅም በማስጠበቅ የተከናወኑ እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ በእንግሊዝና በግብጽ በአውሮፓዊያኑ 1929 የተከናወነውን ስምምነትም ይሁን በግብጽና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የ1959 ስምምነት በወቅቱ ውድቅ አድርጋዋለች።

ስምምነቱ ኢ-ፍትሃዊ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በሚል ውድቅ ከማድረግ ባለፈ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋሟን በማራመድም እስካሁን ዘልቃለች።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 በኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ማካለል ስምምነት በንጉሰ ነገስት አጼ ምኒሊክና በታላቋ ብሪታኒያ መካከል የተፈረመ ቢሆንም በስምምነቱ አንቀጽ ሶስት ላይ ግን የአባይ ጉዳይ መጠቀሱን የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ይናገራሉ።

ታላቋ ብሪታኒያ ''የናይል ተፋሰስ የግዛት አንድነት'' የሚል ዓላማ ታራምድ እንደነበር ጠቅሰው ስምምነቱ ካልተፈረመ የናይል ተፋሰስ በግብጽ ግዛት ስር እንዲሆን የሚል ጫና መፍጠሯንም አቶ ፈቅ አስታውሰዋል።

ስምምነቱ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ አንዳደረገችው የውጫሌ ውል በአማርኛና በእንግሊዘኛ የተለያየ ትርጉም የነበረው ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የብሔራዊ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የሦስትዮሽ ድርድር  ኮሚቴ አባል ኢንጅነር ጌድዮን አስፋው እንዳሉት ኢትዮጵያ ከአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ስትጠቀም የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስታደርግ ቆይታለች።

በአውሮፓዊያኑ 1959 ግብጽና ሱዳን ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላም የአባይን ውሃ ለመከፋፈል ሌሎቹን የተፋሰሱ አገራት በማግለል የውል ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ካርቱም ላይ በመሪዎቻቸው በኩል የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት 10 አንቀጾች አሉት።

እንዚህ አንቀጾች በሶስቱም አገራት ባለሙያዎች በቂ ክርክርና ድርድር የተካሄደባቸውና አሻሚ ትርጉም የሌላቸው መሆናቸውን ኢንጅነር ጌድዮን ያስረዳሉ።

ይሁንና ግብጽ ስምምነቱን ብትፈርምም የአንቀፆችን ትርጉም በማዛባት ጭምር የህዳሴ ግድቡን ውሃ አሞላልና አስተዳደር የሚገድቡ አንቀፆችን ለመጨመር ወደ ኋላ ማፈግፈግ ጀምራለች።

በአውሮፓዊያኑ ቀመር 1997 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣቸው የውሃ ድንጋጌዎችና መርሆዎች ውስጥ ፍትሃዊ ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት አለማድረስ ይገኙበታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታም ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እኤአ በ2015 ካርቱም ላይ ያደረጉትን የመርህ ስምምነትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በ1997 ያወጣው ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ ድንጋጌ መርህን በማይጥስ መልኩ መሆኑን ባለሙያዎቹ አብራርተዋል።

የአባይ ውንዝ በቀን በአማካይ 300 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወይም ከ79 ሚሊዮን ጋሎን በላይ የውሃ ፍሰት እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የ6 ሺህ 695 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ታላቁ የአባይ ወንዝ 11 አገራትን አቆራርጦ የሚያልፍ ሲሆን 86 በመቶ የውሃውን ድርሻ የምታበረክተውም ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም