በአሶሳ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተጀመረ
አሶሳ፣ ግንቦት10/2012 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የኮሮና ቫይረስ የመመርመር ስራ ዛሬ ጀመረ፡፡
የምርመራው ስራ በተጀመረበት ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሃሰን እንደተናገሩት በክልሉ በየደረጃው የሚገኘው ግብረ ኃይል ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
እጅ መታጠብ እና አለመጨባባጥ ቫይረሱን በመከላከሉ የተገኙ ውጤቶች እንደሆኑ ጠቅሰው "አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ ችግር አሁንም ቀጥሏል" ብለዋል፡፡
እንዲሁም ክልሉ ከሱዳን ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ ያለውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴን መቆጣጠር የቀጣይ ትኩረት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከል በተለይም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡትን በመመርመር የቫይረሱን ስርጭት አስቀድሞ ለመከላከል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ በተለይም በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለማቆም ግንዛቤ ፈጠራ እና ህግ ማስከበር ስራ ላይ ትኩረት ማድረጉን አቶ አሻድሊ አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው ዛሬ በአሶሳ ሆስፒታል ሥራ የጀመረው መመርመሪያ ማሽን ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተበባበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀን ከ400 በላይ ሰዎችን የመመርመር አቅም እንዳለው ጠቅሰው ውጤቱን በ24 ሰዓት ማወቅ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
"ለአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ጭምር አገልግሎት መስጠት ያስችላል" ብለዋል፡፡
የመርመራው መጀመር ክልሉ ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስ ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ፣ ነቀምቴ እና ባህር ዳር በመላክ የሚባክነውን ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ጉልበት እና ሌሎች ወጪዎችን እንደሚቆጥብ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በመተከል ዞን ተጨማሪ የምርመራ ማዕከል ለመክፈት ዝግጅት መጀመሩን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በክልሉ መተከል ዞን ለይቶ ማቆያ የነበሩ ሁለት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የፌደራል ጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡