ቀጥታ፡

በቆላማ አካባቢዎች የእርሻ ኢንቨስትመንት የጉልበት ሰራተኛ እጥረት እንዳያጋጥም ጥረት እየተደረገ ነው

ባህርዳር፣ ግንቦት 10/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው ቆላማ አካባቢዎች በኮሮና ምክንያት የጉልበት ሰራተኛ እጥረት እንዳያገጥም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ጥላሁን መኳንንት ለኢዜአ እንደገለጹት በቫይረሱ ምክንያት በእርሻ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች ከማምረት ስራቸው እንዳይደናቀፉ እየተሰራ ነው።

ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር፣ አዊ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም  በሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተርና ሌላም ሰብል የሚመረትባቸው አካባቢዎች  ናቸው።

በነዚህ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በዘር፣ አረምና ምርት መሰብሰቢያ ወቅት በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሰራተኛ ስምሪት ይካሄድ እንደነበር አቶ ጥላሁን አስታውሰዋል።

በኮሮና ተጽዕኖ የጉልበት ሰራተኛ ፣ ለወጭ ንግድና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ሰራተኞች በሚቆዩባቸው ካምፖች አካባቢ የጤና፣ ምግብ፣ መጠለያና ሌሎች የደህንነት ጉዳዮች መሟላታቸውን እየተረጋገጠ መሆኑን  ገልጸዋል።

በተጨማሪም ባለሃብቶች የሚያስፈልጋቸውን የሰራተኛ ብዛት በማሳወቅ ቅድሚያ ከአጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች የሰው ኃይል እንዲያገኙ አሰራር ተዘርግቶ  ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የባለሃብቱ ጥያቄ በአጎራባች አካባቢዎች የማይሸፈን ከሆነ ደግሞ ቀድመው በማሳወቅ ከሌሎች የክልሉ ዞኖች ባለሃብቱ የመሄጃና የመመለሻ ሙሉ ወጪያቸውን በመቻል የሚቀርብበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

ሰራተኛን የማጓጓዝ ስራውም በኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ባወጣው መመሪያ መሰረት ለቫይረሱ በማያጋልጥ መልኩ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የሰራተኛ ስምሪቱን በአግባቡ ለመፈጸምም በየደረጃው ከሚገኙ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፣ ጤና፣ የጸጥታና ትራንስፖርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ኃላፊው አመልክተዋል።

በክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ በበኩላቸው የእርሻ ኢንቨስትመንት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ የህክምና ማዕከል ለማቋቋም ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በሚቋቋሙት ማዕከላት የወባ፣ ካላዘርና ሌሎች በሽታዎችን ከማከምና ከመከላከል ባሻገር የዘመኑ ስጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስ በሰራተኞች ጉዳት እንዳያደርስ  በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አስተባባሪዋ እንዳሉት ለፌዴራል መንግስት በማሳወቅም የህክምና ቁሳቁስና የመድኃኒት አቅርቦት ከወዲሁ እንዲደረግ የጋራ ጥረት እየተካሄደ ይገኛል።

ይህም በእርሻ ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ሰራተኞች የጤንነት ስጋት ሳያጋጥማቸው በመስራት ራሳቸውን ከመጥቀም ባሻገር የሀገሪቱን ልማት እንዲደግፉ ለማስቻል እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም