ቀጥታ፡

''ነጋሪ'' መጽሔት አነጋጋሪ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ጽሁፎችን ይዛለች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የምትታተመው ''ነጋሪ'' መጽሔት አነጋጋሪ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ይዛ ወጥታለች።

መጽሔቷ በአራተኛ ዓመት ቁጥር 12 ዕትሟ ከያዘቻቸው ዓበይት ጉዳዮች መካከል የኮሮና /ኮቪድ 19/ ወረርሽኝን የተመለከተው ፅሁፍ አንዱ ነው።

”ጉልበተኛው ቅንጣት!” የሚል የሽፋን ርዕስ ያገኘው የወቅቱ ዓለም አቀፍ ስጋት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው፤ በርዕሱ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የመከላከል ተግባራትም ተዳሰዋል።

ነጋሪ "መዘናጋት የእግር እሳት" በሚል ርዕስ ኮሮና ያስከፈለውን የሕይወት ዋጋም ታስነብባለች።

መጽሔቷ ኮቪድ19 እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ትተነትናለች፤ ድህረ ኮቪድ 19 የምትኖረውን ዓለም ሁለንተናዊ ገፅታም በምሁራን ሃሳብ ይዛ ቀርባለች።

"የረጅሙ ጉዞ መዳረሻ" እና "ግድብ ላልገደበው ግንኙነት" በሚሉት ርዕሶችም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የተመለከቱ ጉዳዮች ተካተዋል።

"የሱስ ማዕበል" በሚል ርዕስ ደግሞ ሱሰኝነት በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የሚያትት ጸሁፍ ቀርቧል።

በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የዶክተር ካትሪን ሐምሊን የሕይወት ታሪክም 74 ገጾች ባሏት ነጋሪ መጽሔት ተዳሷል።

በ"ነጋሪ" የመሬት አስተዳደርና አርሶ አደሩን የተመለከተ ዘገባም ሽፋን አግኝቷል።

”ነጋሪ” በጥናትና ምርምር፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ ትንታኔና በሞጋች ሐሳቦች የዳበሩ ጽሁፎች የሚቀርቡባት መፅሄት ናት።

ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን፣ የመንግሥት አስፈጻሚዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችንም ተደራሽ ታደርጋለች።

ነጋሪ መጽሔት ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኅትመት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም