አንድ ሺህ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት አባላት ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
አንድ ሺህ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት አባላት ደም ለገሱ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2012 (ኢኤአ) በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የደም እጥረት እንዳይከሰት አንድ ሺህ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት አባላት ደም ለገሱ።
የማህበራቱ አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ዛሬ በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ተገኝተው የደም ልገሳውን ያደረጉት በመንግስት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የደም እጥረት እንዳይከሰትና ደም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በእጥረቱ ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጡ በማሰብ ደም ለመለገስ እንደተገኙ ተናግረዋል።
"አንድም ሰው በደም ዕጦት ምክንያት መሞት የለበትም" በማለት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ደም መለገስ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ማህበራቱ ከዚህ በፊት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ480 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በቀጣይም በተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር አህመድ መሐመድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሽታው በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የተሽከርካሪዎችን የመጫን አቅም፣ የጽዳት ሁኔታ፣ ርቀት የመጠበቅን፣ አፍና አፍንጫን የመሸፈንና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች መሰራቱን ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በተለያዩ በጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ህብረተሰቡን እየደገፉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የላዳ ታክሲ ማህበራት አባላት የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ደም ሊለግሱ መቻላቸውንም ገልጸ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ለሌሎች ማህበራትም ጥሩ ምሳሌ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በሽታውን መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ ሁሉም ሰው ጥንቃቄ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 180 የሚደርሱ የላዳ ማህበራት ያሉ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ አባላት አሏቸው።