የጋምቤላ ክልል ዓመታዊ የጤና ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው

57
ጋምቤላ ሰኔ 28/10/2010 በጋምቤላ ክልል የጤና ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አሳሰቡ፡፡ የክልሉ ዓመታዊ የጤና ጉባኤ በጋምቤላ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሰናይ አኩዎር እንደተናገሩት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የጤና ልማት ሥራዎች ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና የእናቶችና የህፃናትን ጤና በመጠበቅ ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡ በክልሉ በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በየአካባቢው በማሰማራት በተሰሩ ሥራዎችና ህብረተሰቡ ባገኛቸው ግንዛቤዎች በመታገዝ ውጤቱ የተሻለ ሊሆን እንደቻለም ተናግረዋል፡፡ መንግስት የጤና ተቋማትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ለሚያከናውነው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጀምስ ቦል በበኩላቸው በክልሉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ትናንት በተጀመረውና ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ እየተጠናቀቀ ያለውን የበጀት ዓመት የዘርፉ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ከመርሃ ግብሩ የተገኘው  መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም