ባለስልጣኑ 15 ሺህ ጠርሙስ ሳኒታይዘር ጥቅም ላይ እንዳይውል አገደ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ 15 ሺህ ጠርሙስ ሳኒታይዘር ጥቅም ላይ እንዳይውል አገደ
ባህርዳር ግንቦት 9/2012 በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተሰራጨ ከ15 ሺህ ጠርሙስ በላይ ሳኒታይዘር ጥቅም ላይ እንዳይውል ማገዱን በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ቆየ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለስልጣኑ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ያገደው የምርት ጥራታቸው የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው ነው።
አንድ የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ተመርቶ ጥቅም ላይ መዋል ያለበት የአልኮል ይዘቱ 80 በመቶና ከዚያ በላይ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ደረጃ ያስገድዳል ብለዋል ።
ይሁን እንጂ ለክልሉ በስጦታ ጭምር የተሰጡ ሳኒታይዘሮች ባለስልጣኑ ባደረገው የጥራት ማረጋገጫ ልኬት የአልኮል ይዘታቸው ከ26 በመቶ በታች ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
በምዕራብ አማራ በሚገኙ ከተሞች በተደረገ የባለሙያዎች ምልከታ 20 የሚሆኑ ተቋማት አምርተው ያሰራጩት ከ65 ሚሊ ሊትር እስከ አንድ ሊትር መጠን ያለው ከ15 ሺህ ጠርሙስ በላይ ሳኒታይዘር ከደረጃ በታች ሆኖ ተገኝቷል።
ከደረጃ በታች ሆኖ የተገኘው ሳኒታይዘር በህብረተሰቡ ዘንድ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከገበያ ተሰብስቦ እንዲወገድ ባለስልጣኑ ለክልሉ ጤና ቢሮ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጸዋል።
ጉድለት ከተገኘባቸው ተቋማት መካከልም አንዳንዶቹ ባለስልጣኑ በሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ምርታቸውን ፈጥነው እንዳስተካከሉ ተናግረዋል።
ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ተሰራጭተው ጥቅም ላይ ቢውሉ ህብረተሰቡ ራሴን ጠበቅኩኝ ብሎ በመዘናጋት ለኮሮና ቫይረስ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ጥራት ቁጥጥር የስራ ሂደት ተወካይ ኃላፊ አቶ መንበሩ ፍፁም በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅን ደጋግሞ በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም የአልኮል መጠናቸው ከ80 በመቶ በላይ የሆኑ ሳኒታይዘሮች መጠቀም የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ይመከራል ብለዋል ።
ባለስልጣኑ የጥራት ችግር ያለባቸው ሳኒታይዘሮችን ቢሮው በተዋረድ ባሉት መዋቅሮቹ ሰብስቦ እንዲያስወገድ በጠየቀው መሰረት ጉዳዩ ለበላይ አመራሮች ቀርቦ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
በቀጣይም ቢሮው ከባለስልጣኑ ጋር በመሆን የጥራት ችግር ያለባቸውን በመቆጣጠር ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በሃገር ደረጃ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፈቃድ ወስደው የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር የሚያመርቱ ከ110 በላይ ተቋማት መኖራቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።