በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ተጀመረ
ባህርዳር ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች "ታክሲየ" በሚል በሞባይል መተግበሪያ የታገዘ የሜትር ታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀመረ።
በባህር ዳር ከተማ የአገልግሎቱ መጀመር ዛሬ ይፋ በተደረገበት ስነስርዓት ወቅት የከተማው አስተዳደር ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው አለኽኝ እንዳሉት የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑ ከተሞች የሜትር ታክሲ አገልግሎት መጀመሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
"ሜትር ታክሲ" የከተሞችን የትራንስፖርት ዘርፍ ከማዘመን ባለፈ ተገልጋዮች ካሉበት ድረስ ደህንነታቸውን የጠበቀ አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
አገልግሎቱን ያመቻቸው አካል በቀጣይ የተሻለ ተሞክሮ በማምጣት የከተማው ህብረተሰብ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጠቀም መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
በከተማዋ ዛሬ የተጀመረው አዲሱ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጽህፈት ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ኤል ታክሲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ ሙሏለም በበኩላቸው "ታክሲየ" ለህዝቡ የተቀላጠፈ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በታክሲየ የሞባይል መተግበሪያ ወይም በ6124 ጥሪ ማዕከልን ተጠቅሞ በመደወል አገልጋይና ተገልጋይን በቀላሉ በማገናኘት የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎቱን እንደሚሰጥም አስረድተዋል።
ተገልጋዮች ከዚህ በፊት ያጋጥማቸው የነበረን ያልተገባ ክፍያና እንግልት በማስቀረት ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሆነም ገልፀዋል።
ለዚህም ኩባንያው ከባህርዳር ከተማ አነስተኛ ሆቴል እና "ኤርፖርት ታክሲ "ባለንብረቶች ማህበርና ከተለያዩ የባጃጅ ማህበራት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ወስዶ ወደስራ መግባቱን አስታውቀዋል።
በክልሉ በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች ዛሬ የተጀመረው የሜትር ታክሲ አገልግሎትን በቀጣይም በደሴና ሌሎች የክልሉ ከተሞች ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግምጠቅሰዋል።
በሁለቱ ከተሞች 68 የኤርፖርት ታክሲዎችና 100 ባጃጆች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የባህርዳር ከተማ አነስተኛ ሆቴልና ኤርፖርት ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ መናን ከማል የአገልግሎቱ አባል በመሆናቸው የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
ወጥ የሆነ ክፍያ ደንበኞችን በማስከፈል ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ካሉበት ድረስ በመሄድ እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ ስነስርዓት የማህበሩ አባላትና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።