የማህበራዊ ተጠያቂነት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማህበራዊ ተጠያቂነት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2010 ዜጎች አገልግሎት የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የማህበራዊ ተጠያቂነት ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተገለፀ። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት ማጠናቀቂያ ላይ ዛሬ ውይይት ተደርጓል። የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሁለት ከአየርላንድ፣ ከኦስትሪያና ከዓለም ባንክ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ 223 ወረዳዎች ላይ በአገልገሎት ሰጪዎችና ተገልጋዮች መካከል በመሆን ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ የግንዛቤና የስልጠና ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ በላይ አስራት እንዳሉት ፕሮግራሙ መሰረታዊ የአገልግሎት ማሻሻያ ስር ያለ ፕሮግራም ሆኖ ሁለቱን አካላት በማወያየትና ግልፀኝነት በመፍጠር አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ በሚያስችል መልኩ መሰራቱን ገልፀዋል። ህብረተሰቡ ጥያቄዎችን ማንሳት መጀመሩ በአገልግሎት ሰጪው በኩል ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴዎችን መፍጠሩን አሳውቀዋል። ተገልጋዩ ከአገልግሎት ሰጪው ጋር የነበረው ግንኙነትም የተቀራረበ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። ፕሮግራሙ አሁን ላይ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የሚተገበር ሲሆን ስራውን የሚሰሩ ከ100 በላይ የማህበረሰብና የእርዳታ ማህበራት ተሳታፊዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። በተለይ አቅም የሌላቸው ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች እኩል የአገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የማህበረሰብ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመሆን ተጠቃሚነታቸው ላይ በመስራት ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል ነው የተባለው። በፕሮግራሙ የአቅም ልማትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ መስከረም ግርማ በሰባት አመት የፕሮግራሙ ወቅት በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በውሃና በገጠር መንገድ ላይ ሲሰራ የቆየ መሆኑን ገልፀዋል። ህብረተሰቡ በተሰጠው ግንዛቤ አገልግሎት የማግኘት መብቱን የመጠየቅ፣ በቡድን በመሆን በጋራ አገልግሎቶችን የመገምገምና እንዲስተካከሉ የመጠየቅ እንቅስቃሴም እድገት አሳይቷል ብለዋል። ተገልጋዩ ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ባለው የገፅ ለገፅ ውይይት የአገልግሎት ክፍተቶች እንዲሟሉ መጠየቅ በመቻሉ ከበጀት ምደባ ጀምሮ አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው ልክ (ስታንዳርድ) እንዲሰጡ ከማድረግ አንፃር መሻሻሎች እንደታዩ ነው የገለፁት። የቢሾፍቱ የ23 እድሮች ፎረም ሰብሳቢ አቶ አያሌው ከለላው ፕሮግራሙ በመሰረታዊ አገልግሎቶችና ፍላጎቶች ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲመጣ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። አገልግሎት ሰጪው ከህብረተሰቡ ጋር ባለው የውይይት ጊዜ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ውክልና ያለው ተገኝቶ ሃሰቡን በመግለጽ በዚያ መሰረት ታቅዶና በጀት ተመድቦ ተግባራዊ እንዲሆን በጋራ የመስራት አቅምን ፈጥሯልም ብለዋል። በህብረተሰቡ ጥያቄ በተቆፈሩ ሁለት ግዙፍ የውሃ ጉድጓዶች ምክንያት ለብዙ ጊዜያት በከተማዋ ይታይ የነበረው የውሃ እጥረት ተቀርፈዋል ሲሉም አስረድተዋል። በሌላ በኩል በአንድ ክፍል ውስጥ ከ80 እና 90 በላይ ሆነው ተጨናንቀው እንዲማሩ ይገደዱ የነበሩ ተማሪዎችን በስታንዳርዱ መሰረት የክፍል ጥመርታ ለማስተካከል በፕሮግራሙ በኩል ባለሶስት ፎቅ የህንፃ ግንባታ በማከናወኑ ችግሩ ተፈቷልም ብለዋል። የማህበራዊ ተጠያቂነት አሁን ከሚሰጣቸው ዘርፎች በተጨማሪም በሌሎች ዘርፎች ላይ መስራትና መስፋት እንዳለበት ገልጸው በተለይ የመብራት ችግርም መታየት እንዳለበት አሳውቀዋል። የማህበራዊ ተጠያቂነት ሁለት ከ2003 ጀምሮ ለሰባት አመታት ሲተገበር የቆየ ሲሆን ሶስተኛውን ምዕራፍ በ2011 ዓ.ም ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል።