በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች 41 የታካሚዎች መከታተያ መሳሪያ ሊልኩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች 41 የታካሚዎች መከታተያ መሳሪያ ሊልኩ ነው
ግንቦት 8/2012(ኢዜአ) በቻይና ትምህርት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባሰባሰቡት ገንዘብ 41 የታካሚዎች መከታተያ ስክሪን ገዝተው ለመላክ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ መንግስት እየወሰደ ያለውን የመከላከልና የመቆጣጠር እርምጃ ለመደገፍ በቻይና በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር 98 ሺህ 984 ዩዋን አሰባስበዋል፡፡
በተሰበሰበው ገንዘብ የተገዛውን የታካሚዎች መከታተያ ስክሪኖች ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ለጉምሩክ ማሟላት ያለባቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገቢውን ለማሰባሰብ የተቋቋመው የተማሪዎች ማህበር ገልጿል።
በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የተገዙት የህክምና መሳሪያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከላከል ባለፈ ለማንኛውም ታካሚ እንዲሁም ለፅኑ ህሙማን እና ከቀዶ ጥገና በኅላም የሚያገለግሉ መሳሪያዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
የታካሚ ጤና መከታተያ መሳሪያዎቹ ሀገሪቱ በዚህ ወቅት ያለባትን የህክምና መገልገያ መሳሪያ ችግር በተወሰነ መልኩ የሚቀርፉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህንን በጎ ተግባር ለማስቀጠል የሁለተኛ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀምሩ የገለጸው ማህበሩ፤ በሚሰበሰበው ገንዘብም ተጨማሪ የህክምና መሳሪያዎች ገዝተው ለመላክ እንዳቀዱም ጠቅሷል።
ማህበሩ ድጋፍን ላደረጉ በቻይና በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች እና በእረፍት ሀገር ቤት ያሉትን ተማሪዎች አመስግኗል፡፡
በሁለተኛ ዙር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መሳተፍ የሚፈልጉ በየትኛውም አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የማህበሩን አባላትን በማነጋገር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዲችሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህንን በጎ ተግባር እንዲያከናውኑ ከጎናቸው በመሆን አብረው እየሰራ የሚገኘውን በቻይና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ማህበሩ ምስጋና አቅርበዋል።
በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ በራሳቸው ተነሳሽነት፤በተማሪዎች ሕብረት እንዲሁም በአስተባባሪዎች አማካኝነት “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል ከዕለት ወጪያቸው ቀንሰው ከወገን ጎን በመቆማቸው ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
ከዚህ በፊትም በቻይና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ግዢ የሚሆን ድጋፍ በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውንም ኤምባሲው አስታውቋል።