ግብፅ በከርሰ ምድር ውሃ ሃብቷ የተሻለች አገር ሆና እያለች በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የተሳሳተ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ግብፅ በከርሰ ምድር ውሃ ሃብቷ የተሻለች አገር ሆና እያለች በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የተሳሳተ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2012 (ኢዜአ) ግብፅ በከርሰ ምድር ውሃ ሃብቷ ከኢትዮጵያ የተሻለች አገር ሆና እያለች በአባይ ላይ የያዘችው አቋም ግን የተሳሳተ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና መገናኛ ብዙሃንም በመጠቀም ይህን እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ በጉልህ ልታንጸባርቅ ይገባል ብለዋል።
የምድራችን ረጅሙን የአባይ ወንዝ 86 በመቶ የውሃ መጠን የምታበረክተው የጥቁር አባይ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ መሆኗ ይታወቃል።
በተፋሰሱ አገራት መጨረሻ ላይ የምትገኘውና ወንዙን ለሁለንተናዊ ግልጋሎት የምትጠቀመው ግብፅ 'አባይ የግሌ ስጦታ ነው' በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ትርክቷ አሁንም ቀጥላበታለች።
ዓለማችን በአዲስ ወረርሽኝ ተሸብራ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንኳን ኢትዮጵያ ለታዳሽ ሃይል ማመንጫነት የምትገኘውን ታላቁን የሕዳሴ ገድብ ለማሰናከል ከመሞከር አልቦዘነችም።
ግድቡ ከፍጻሜ እንዳይደርስና ውሃ እንዳይሞላ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲና የሚዲያ አቅሟን በመጠቀም ጫና ለማሳደር ጥረት ላይ ትገኛለች።
በእርግጥስ 'አባይ የደማችን ጠብታ ነው፤ አባይ የሕልውናችን መሰረት ነው' እና ሌሎችንም ነባር ብሂሎች በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር አጠናክራ የመቀጠሏ ምስጢር ከእውነተኛ አመክንዮ የመነጨ ነው?
የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ዘርፍ ምሁሩና የፓን አፍሪክ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ገብረጊዮርጊስ ግብፅ ለዘመናት ይዛው የመጣችውና አሁንም የያዘቸው አቋም በእውነት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ያብራራሉ።
'አባይ የደማችን ጠብታ ነው' የሚለው የግብጻዊያን አባባልም ከእውነት የራቀ በአሜሪካዊያንም ሆነ በግብጻዊያን ምሁራን ጥናት የተረጋገጠው ግብፅ ለቀጣይ 500 ዓመታት የሚያገለግል የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት መሆኗን ይናገራሉ።
ይህም በከርሠ ምድር ውሃ ሃብት ረገድ ከኢትዮጵያም ሆነ ከቀጣናው አገራት በላይ መሆኑን ገልጸው፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ የሚገኘው የከርሠ ምድር ውሃ ሀብት ከግብፅ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብጽ የቀይ ባሕር የውሃን አጣርቶ ለመጠቀም ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ግብጽ የከርሰ ምድር ሃብቷን ከመጠቀም ይልቅ በአባይ ወንዝ ላይ ብቻ በመንጠልጠልና የኢትዮጵያንም በተፈጥሮ የመልማት መብቷን እየተጋፋች እንደሆነ ይገልጻሉ።
እስካሁን በተደረጉ የድርድር ሂደቶች ላይ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች በኩል ይህ ጉዳይ ጎልቶ ያልተነሳ ነጥብ እንደሆነም ያምናሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት ዲን ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ደግሞ "የግብፅና የሱዳን ሚዲያዎች አዲስ ምዕራፍ ተሻግረዋል" የሚል እምነት አላቸው።
"በዚህ ወቅት ከአባይ በላይ አጀንዳ ሊኖር አይገባም" ይልቁንም፤ በግብጽ በኩል ምድር ላይ ያለውን እውነታ አጉልቶ ለማሳየት መገናኛ ብዙሃን የጎላ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን በአባይ ጉዳይ ስራዎቻቸው የአንድ ወቅት የዘመቻ ስራ እንጂ፣ በተከታታይና በጥልቀት በተቀናጀ አግባብ ሃላፊነታቸውን የመወጣት ችግር ውስጥ እንደሆኑ አስረድተዋል።
በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን እንደ አባይ ጉዳይ 'ሚዲያ ፎረም' በመመስረት በመቀናጀት ለወዳጅም ሆነ ጠላት ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በሚያደርግ አግባብ በተለያዩ ቋንቋዎችና አቀራርቦች መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ዶክተር ሰለሞን በበኩላቸው ግብጽ በማንኛውም ጫና ውስጥ ብትሆን የአባይ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ አጀንዳዋ ነው፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ይህ እየተስተዋለ አይደለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች "ወንዙን ግብጽና ሱዳንን ለመጉዳት አንጠቀምም" ከሚለው የተለመደ አመክንዮ በተጨማሪ፤ ግብጽ ስላላት የውሃ ሃብትና ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማጉላት አለባቸው ብለዋል።
በመንግስት፣ በህዝቡና በፖለቲከኞችም ዘንድ ቀዳሚው ትኩረት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው።
በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያን፣ ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ዓለም አቀፍ ተቋማትንና ማህበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ ዲፕሎማሲያዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንዳልሆነም ገልጸዋል።
"ሚዲያ ለአንድ አገር ዲፕሎማሲ መሰረት ነው" የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ በግብጽ እንደሚደረገው ሁሉ የኢትዮጵያ ሚዲያም የውሃ ምሁራንን በመጠቀም መረጃ መለዋወጥና ማድረስ እንደሚገባቸው ተናገረዋል።
ይህም ሚዲያው የዲፕሎማሲ አቅሙን እንዲወጣና ተደራዳሪዎችን አቅም የሚፈጠር ነው ይላሉ።
የአባይ ጉዳይ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ በር የሚያንኳኳ ቢሆንም በውስጣዊ ፖለቲካ ሳቢያ የሚጠበቀውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠው ገልጸው፤ "የፖለቲካ ጉዳይ ነገ ይፈታል፣ የአባይ ጉዳይ ግን የትውልድ የሚተርፍ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት" ብለዋል።
ኢትዮጵያም ከግብጽ ከወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በማሳደግ የሃይል ሚዛን ማስጠበቅ እንደሚገባት ተናግረዋል።
በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ የግልም ሆነ መንግስታዊ መገናኛ ብዙኅን ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ሚዲያዎች ጋር ግንኙነትን ፈጥሮ በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማትና የዘርፉ ምሁራን ሚዲያውን መመገብ፣ መንግስትም ለዚህ ዘርፍ ድጋፍ ማድረግና ዘርፉን በዘላቂነት የሚመራ አካል አቋቁሞ መስራት እንዳለበት ያምናሉ።